ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከልን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የሚያግዝ ሕዝባዊ ውይይት ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተጀምሯል በተባለበት ሁኔታ ከ100 በላይ ዜጎች መገደላቸው ተመልክቷል።
አስተማማኝ የሆነ ጸጥታ በራቀውና ቀጥተኛ የሆነ ተደጋጋሚ ዘር ተኮር ጥቃት የሚታይበት በመተከል ዞን የታጣቂዎች ጥቃት ዙሪያ ጉዳዮ ይመለከታቸዋል የተባሉ አካላት ተሳታፊ እየሆኑ ነው ተብሏል።
የጉባዔው ዋነኛ ዓላማ የመተከልን ሰላም መመለስ በሚቻልበት ዙሪያ ለመምከር መሆኑን የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክልሉ የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሳ ሃሚድ ገልጸዋል።
በመተከል በተለይ በአማራና በአገው ተወላጅ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው በንብረትና በህይወት ላይ የሚፈጸም አሰቃቂ ግድያ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን የፌደራል መንግስትም ሆነ የክልሉ መንግስት ሁኔታውን ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ጥረት እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ለመባባሱ ወነኛ ምክንያት መሆኑ ተመልክቷል።