ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የቤኒሻንጉል ጉሙዝ መንግሥት በመተከል ዞን ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የተባሉ ሥድሥት አመራሮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰማ።
የኢፌዴሪ ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ የነበሩት አቶ ቶማስ ኩዊ፣ የቀድሞው የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አድጎ አምሳያ፣ አቶ ሽፈራው ጨሊቦ፣ የቀድሞ የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር፣ የመተከል ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ባንዲንግ ማራ፣እንዲሁም አቶ አረጋ ባልቢድ የመተከል ዞን የቀድሞ አመራር የነበሩ በጥፋተኝነት የተያዙ ባለሥልጣናቶች ናቸው ተብሏል።
በተያያዘ ዜና ይህንን ዘግናኝ ጥቃት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመከላከያ ሠራዊቱ በሰጡት አስቸኳይ ትእዛዝ በስፍራው በሚገኙ ታጣቂዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ታውቋል።
እስካሁን ድረስ መከላከያ ሠራዊቱ በወሰደው እርምጃ ከአርባ በላይ ታጣቂዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ሌሎች በርካታ ታጣቂዎች እንደተማረኩ በመንግሥት በኩል ከተሰጠው መግለጫ መረዳት ተችሏል።