የአክሱም ጫፍ አቁማዳ || ደበበ ሰይፉ

የአክሱም ጫፍ አቁማዳ || ደበበ ሰይፉ

ትግራይ ላከ ወሎጋ አበድረኝ ብሎ አንድ ቁና ጤፍ
ወሎም አፈረና የለኝም ማለቱን ባህሉን መዝለፍ
ቆሌውን መንቀፍ
ላከ ወደሸዋ ምናልባት ቢሰጠው ለሰው እሚተርፍ።
ሸዋም አፈረና የለኝም ማለቱን
ወደ ሐረር ዞረ
ሐረርም መልሶ ባሌን አተኮረ
ባሌም ወደ አርሲ፤ አርሲ ሲዳሞን
ሲዳሞም ተክዞ፤ ግን የለኝም ብልስ ማን ያምነኛል ብሎ
ወደጋሞ ላከ አቁማዳ ጠቅሎ።
ጋሞን ብርድ መታው ሐዘን ገባውና
የራሱን ምንዳቤ የግል ስቅየቱን ችሎት በጥሞና
በጋቢ ደቡኖ የልቡን ጠባሳ ሲኖር እንደደህና
ዛሬ የወንድሙን የእርዳኝ አቤቱታ መስማት አልቻለና።
አውጥቶና አውርዶ ላከ ወደ ከፋ እጅግ አስተዛዝኖ
ከሀፍረት ያድነኛል፤ ከረሃብ ያወጣኛል
ሲል በአያሌው አምኖ።
ከፋ እንደደረሰው
በድንገት አቁማዳው በነብሱ ዋይታ
ሐራራው ተሰማው የሥጋው ድንፋታ
በብልሀት አዛጋ ቆይቶ ቆይቶ
የተስፋ ጥል ቀዳ
ሲልክ ከኢሉባቦር አበድረኝ ብሎ እህል በአቁማዳ።
ጭምቱ ይሉባቡር ይኖር የነበረ የቤቱን ጉድ ጓዳ
በሞኛሞኝ ገላው ቆዳው ውስጥ ወሽቆ
ጠየቀ ወለጋን ሐፍረቱን ደብቆ
ኩራቱን ዘቅዝቆ።
ኬት አመጣ ብሎ ወደኔ ላከብኝ
እያለ ወለጋ
እጅጉን ተደሞ
ሄደ ወደ ጎጃም
ዛሬን ሁነኝ ብሎ ሊማፀነው ቁሞ።
ጎጃምም ተሰምቶት፤ ሰቀቀን ሐዘኑ፤
ደረት እየመታ፤ ቅኔ እያወረደ፤
እንባ እያፈሰሰ
ወግና ኩራቱን በየሜዳው መሀል እየነሰነሰ
ዐባይን ተሻግሮ ከጎንደር ደረሰ።
ፋሲል ላይ ተነጥፎ፤
ጎንደርም ሐዘን ላይ ነበረ ተቀምጦ
ተድላ ልጁ ሙቶ፤ ገና ክንዱ ታጥፎ፤ በዘመን ተድጦ
ጎጃም መጣ ሲሉት
የእዝን የተመኘ ልቡን በታዘበ
የኩራት ካባውን ሊጥል ባንዣበበ
የወንድሙ መምጣት፤ እቅጩ መንስዔ፤
መሆኑን ሲረዳ ረሀብ አበሳ
ጥንትም አልሆነኝም
ከእንግዲህ ይበቃኛል ለይሉኝታ አልሳሳ
ብሎ ከኤርትራ እህል ለመበደር በርትቶ ተነሳ።
የዘመዱ እጦት ነበርና እጦቱ
በዝቶ ሰቀቀኑ
ኤርትራ ታመመ ደም ጎረፈ ከዓይኑ፡፡
ወደትግራይ ላከ መላ ባገኝ ብሎ ከአደራ ደብዳቤ
“እባክህ ላክልኝ አንድ አቁማዳ እህል ልሞትነው ተርቤ።”
ትግራይ አስተውሎ
አቁማዳው የራሱ መሆኑን ለይቶ
ረሀብ ዕጣቸው የሁል ወንድሞቹ መሆኑን አካቶ
ሐዘኑ አነቀው፤ ትንፋሹ መረረው፣ ትካዜ ሆዱገብቶ።
“እኔና ወንድሞቼ” አለ በለዘብታ
ለራሱ እንዲያወራ የራሱን ስሞታ፤
“እኔና ወንድሞቼ ሁላችን . . . ሁላችን
ከባዶ አቁማዳ ነው እሚዛቅ ፍቅራችን
ይህ ነው አንድነታችን
ይህ ነው ባህላችን
ዘመን ማዛጋቱ በያንደበታችን።
ለኋላ ትውልዶች ተረት እንዳይመስል ይህ ብካይ እሮሮ
ይህ ጠፍ ስብእና ይህ ስቃይ አእምሮ
እንዳኖረው ያሻኛል ይህንን አቁማዳ ከፍ ካለስፍራ
መጥቆ እንደባንዲራ
ምንም ባዶ ቢሆን
በውስጡ አይጠፋና የታሪክ አዝመራ።
ይህንን ተናግሮ
ከአክሱም ሐውልት ዘንድ ትግራይ ተጠግቶ
አንዴ እየፀለየ አንዴ እየዘመረ ያለመጠን ተግቶ
ጫፉ ላይ ሰቀለው ያን አቁማዳ አውጥቶ።

LEAVE A REPLY