ክቡራን ወዳጆቼ || ሰረጸ ፍሬስብሓት

ክቡራን ወዳጆቼ || ሰረጸ ፍሬስብሓት

የካህኑ፣ የጉባኤ መምህሩ፣ የሊቁ አባቴ የሊቀ ኅሩያን ፍሬስብሐት ዜና ዕረፍት ከተሰማበት ሰዓት ጀምሮ፣ እኔንም መላውንም ቤተሰብ ለማጽናናት በሚያመቻችሁ መንገድ ኹሉ ስለደከማችሁልኝ፣ የበጎነታችሁን ብድራት በፍፁም የማያስቀር አምላክ የምትሹትን ኹሉ ይሰጣችሁ ዘንድ እለምናለሁ።

የሊቁ አረጋዊ አባት ስንብት፥ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ክብረ በዓል (ንግሥ) ይመስል ነበረ እንጂ፣ በፍፁም “የቀብር ሥነ ሥርዓት” የሚባል አልነበረም። የገነተ ኢየሱስ እና የገነተ ማርያም ሊቃውንት ሌሊት፥ በማኅሌት፣ በጸሎተ ፍትሐት እና በሰዓታት፤ ጠዋት፥ በቅዳሴ መድከማችው አንሶ፤ ጠዋት ደግሞ፤

“ወተቀበልዎ መላእክት በስብሐት ወበባርኮት፤
ወአብእዎ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፥ አብእዎ
ለገብረ መስቀል (ፍሬስብሐት)።”

እያሉ የሰማያትን ዝማሬ እያሰሙ፣ እየወረቡ፤ ሊቁ ወንድማቸው የደስታ፣ የክብር፣ የጽድቅ አክሊል መቀዳጀቱን አብሥረው፥ እግዚአብሔርን ከፍ አድርገው አመስግነውልናል።

የገነተ ኢየሱስ እና የገነተ ማርያም ታቦታተ ሕገጋት ከመንበራቸው ተነስተው፣ ዕድሜውን ሙሉ ያከበራቸውን፣ በፍፁም ትኅትና የታዘዛቸውን ካህን በዐውደ ምሕረት ዑደት ሸኝተውታል።

ጥዑመ ልሣኑ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አባታችን አቡነ ናትናኤል ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት በዚህ ታላቅ የስንብት መርኀ ግብር ላይ፣ የኔታ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ፤ የሊቃውንቱን የወረብ ኃይለ ቃል ከቅዱስ ያሬድ ዚቅ የተመረጠውን መሠረት አድርገው፣ ነፍስ ድረስ ዘልቆ የሚሰማ ትምህርት አስተምረውናል።

ከእርሳቸውም በመቀጠል፥ ሊቁ ወንድሜ ሙኀዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ “በምድር የማይጠናቀቁ፣ በሰማይ እንደገና የሚቀጥሉ ኹለት ተግባራት ‘ዝማሬ እና ክህነት’ ናቸው።” ካለ በኋላ፤
“የካህን ምድራዊ ሞት፤ የሰማያዊው አገልግሎት
መሸጋገሪያው ወይም የቤተ መቅደስ ለውጥ ነው።
ከምድራዊው ቤተ መቅደስ ወደ ሰማያዊው ቤተ
መቅደስ ተሸጋግሮ ግልጋሎት መቀጠል ማለት ነው።
ድካም የሌለበትን፣ የጊዜ ወሰን የሌለውን ግልጋሎት
በሰማያት መቀጠል ማለት ነው።” በማለት፥ ኹላችን የማናስተውለውን ታላቅ ምሥጢር ገልፆልናል።

የሊቀ ኅሩያን ፍሬስብሐት የሕይወት ታሪክ፤ እርሱ በሕይወት ዘመኑ ያስጠነቅቅ በነበረው እና በሚወደው ልክ፣ ያለ ምንም የማሳመሪያ እና የማጋነኛ ቃል እውነቱ ብቻ እንዲነገርለት እንደሚፈልገው (በተፈጥሮው ጩኸት እና የሚጋነን ነገር አይወድ እንደነበር ልብ ይሏል፤) ተዘጋጅቶ፤ በወዳጁ በቀሲስ ሙላት በርቱዕ ንባብ ቀርቧል።

ይህንን ሥሙር መርኀ ግብር በቃለ ምዕዳን እና በሠርኆተ ሕዝብ ያሣረጉት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ነበሩ። ብፁዕ አባታችን በሕይወት ዘመኔ ኹሉ የማልረሣው ኃይለ ቃል አስተምረው፤ “እትዉ” በሰላም ብለው ሕዝቡን አጽናንተዋል።

የዚህ ኹሉ፤ ሥነ ሥርዓት የክብር መሪ፣ አስተጋባኢ፤ እጅግ የማከብረው መምህሬ፣ ወንድሜ እና አለቃዬ፥ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ ነበር። የቤተ ክርስቲያንን ለዛ በጠነቀቀ ሥነ ሥርዓት፤ ማዕርጋትን ሳያዛንፍ እና ሳያቀዳድም ግሩም አድርጎ ሙሉ ሥርዓቱን መርቶታል።

ሥነ ሥርዓቱ እንዲህ ያማረ እንዲኾን፤ የደከማችሁ የአባቴ ወዳጆች፤ የደብራችን አስተዳዳሪ አባ ቆሞስ ነአኲቶ፣ የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ አባታችን።
እነ አብርሃም ፈቃደ ሥላሴ፣ እነ አሐዱ ሰሎሞን፣ እነ መኮንን ይመር፣ እነ መምህር ደረጀ፣ እነ ዐምደ ብርሃን ኃይለማርያም፣ እንዲሁም ስማችሁን ዘርዝሬ የማልጨርሰው የገነተ ኢየሱስ ገነተ ማርያም መሠረተ ሃይማኖት ሰንበት ተማሪዎች፤ ክበሩልኝ፣ ከቅዱሳን በረከት አይለያችሁ እላለሁ።

ለዚህ ኹሉ ክብር፣ ለዚህ ኹሉ ፍቅር፣ ለዚህ ኹሉ የልብ ቅንነት የሚመጥን የምስጋና ቃል በእውነቱ የለኝም። የእነዚህን ታላላቅ ሰዎች እና በሥርዓቱ ላይ የተገኛችሁ እንዲሁም በተለያየ ኹኔታ ውስጥ ኾናችሁ በመንፈስ ከእኔ ጋር የነበራችሁ ወዳጆቼን የማመሰግንበት ብቁ ዐንደበት የለኝም። አባቴን ይህን በመሠለ ኀዘንን ፈጽሞ በሚያስረሣ ክብር ስለሸኛችሁልኝ፣ እርሱ ኃያሉ እግዚአብሔር ብድራታችሁን ይክፈልልኝ!!!
===አሜን===

LEAVE A REPLY