ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በመጪው የግንቦት በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ከሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የአዲስ አበባና የነዋሪዎቿን ጥቅም ማስከበር ዋነኛ አጀንዳዬ ነው እያለ ነው፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎች የድርጅቶቹን አመራሮች ለማስፈታት ለአምስት ቀናት የሚቆይ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ የጀመረው ባልደራስ በዋና መዲናዋ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ አለኝ ብሏል።
በሥድሥተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ዋነኛ አጀንዳዬ የአዲስ አበባ እና የነዋሪዎቿን ጥቅም ማስጠበቅ ነው ያለው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ፤ ለዚህ ደግሞ ከተማዋ በራስ ገዝ መተዳደር አለባት የሚል አቋም ይዟል።
“ለዚህም ብቻዬን አይደለሁም፣ ይህንኑ ሐሳብ ከሚደግፉ ሌሎች ፓርቲዎች ጋር እየሠራሁ ነው” ያለው በእስክንድር ነጋ የሚመራው ፓርቲ፤ በቀጣዮ ምርጫ ውጤታማ ሊያደርጉኝ ይችላሉ ያላቸውን ሥራዎች ከወዲሁ እየሠራሁ ነው ብለዋል።