ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በተለያዮ ሀገራት እየተከሰተ ያለው አዲስ የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በደቡብ አፍሪካ፣ በናይጄሪያ፣ አሜሪካ፣ በእንግሊዝ ሃገር ከተገኘው የቫይረሱ ዝርያ የተለየና አዲስ አይነት የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በቅርቡ መከሰቱ በዚህ ወቅት እየተነገረ ነው።
የቫይረሱ ዝርያ ከመጀመሪያው ቫይረስ ጋር ሲነጻጸር የህመም ደረጃን የመጨመርም ሆነ ለሞት የማጋለጥ እድሉ ምን ያክል እንደሆነ በጥናት ያልተረጋገጠ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ቫይረሱ ወደ ሀገሯ እንዳይገባ ከወዲሁ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረግሁ ነው ብላለች።
አዳዲሶቹ የቫይረሱ ዝርያዎች በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው የመዛመትና የመተላለፍ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን የጠቆመው የጤና ሚኒስቴር፤ በተለይም በደቡበ አፍሪካና በናይጄሪያ የተገኙት የቫይረሱ ዝርያዎች ከቅርበት አንጻር ለኢትዮጵያ ስጋት ስለሚሆኑ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራበት ነው ብሏል።