ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች በጥር ወር መገባደጃ ላይ በእነርሱ ላይ የሚቀርቡ ምስክሮችን መስማት እንዲጀመር ፍርድ ቤቱ ወሰነ።
“በቅድሚያ ከአራት ወራት ቀጥሮ አሻሽላችሁ ለጥር 5 በማድረጋችሁ አመሰግናለሁ። ግን አሁንም ከጥር 26 ጀምሮ አስከ የካቲት 28 ድረስ ምስክር ለማሰማት በሚል ፍ/ቤቱ ያስቀመጠው ትክክል አይደለም ” በማለት የተናገረው የባልደራስ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ የተፋጠነ ፍትህ እንፈልጋለን፣ በምርጫ ተወዳድረን ሕዝብ እንዲዳኘን እንሻለን። በመሆኑም ቀጠሮው ይስተካከልልን ሲልም ችሎቱን ጠይቋል።
ታከለ ኡማን አስጨንቀኸል የሚል ክስ የተመሠረተበት ሁለተኛ ተከሳሽ ስንታየሁ ቸኮልም፤ ” እኔ አሁንም እደግመዋለሁ እኛ ሰው ገለን አይደለም፣ ጄኖሳይድም ፈፅመን አይደለም፣ ሕዝብ እንዲራብ እንዲጠማ፣ እናቶች እንዲያለቅሱ አድርገን አይደለም እዚህ የታሰርነው። ይልቁንስ ህዝብን ስለመገብን ጄኖሳይድ እንዳይከሰት ስለተከላከልን፣ ለግፉሃን እና ለጭቁኖች የተሻለ ሐሳብ ይዘን ድምፅ ስለሆንን ብቻ ነው። በመሆኑም አሁንም ሕዝብ በየቦታው እየታረደ ነው፣ ጄኖሳይድ እየተፈፀመ ነው። ነገ የተሻለ ሐሳብ ለሐዝቡ በማቅረብ እና በምርጫ ተወዳድረን አገሪቱ አሁን ከገባችበት አረንቋ ማውጣት እንፈልጋለን። ስለዚህ አሁንም የቀጠሮ ቀን ይሻሻል።” በማለት አቤቱታውን አቅርቧል።
ሦስተኛ እና አራተኛ ተከሳሽም በተመሳሳይ ሐሳባቸውን በመግለጽ ሀያ ይደርሳሉ የተባሉ ምስክሮችን በቀን አንድ ምስክር ብቻ ይሰማ የሚለው አካሄድ ሆን ተብሎ ጊዜ ለማጎተት የታለመ ነው በማለት ቢቃወሙም ዳኞች ግን ከጥር 26 ጀምሮ የምስክሮች ቃል መሰማት ይጀምር ሲል ትእዛዝ ሰጥተዋል።