ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በየዓመቱ የሀገራትን ወታደራዊ አቅም ይፋ በሚያደርገው ዓለም ዐቀፍ ተቋም ኢትዮጵያ ዘንድሮ ከአፍሪካ ሥድሥተኛ ደረጃ ተሰጥቷታል።
ግብፅ ከአፍሪካ ቀዳሚ ስትሆን አልጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ሞሮኮና ኢትዮጵያ በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል፤ ሱዳንም 10ኛ ደረጃ አግኝታለች።
ግሎባል ፋየር ፓወር በዓለም ዙሪያ ካሉ አገራት መካከል ባደረገው የወታደራዊ ጥንካሬ ምዘና፣ ከ50 በላይ መመዘኛዎችን የተጠቀመ ሲሆን በዚህም አገራት ያላቸውን የወታደራዊ ኃይል ጥንካሬ በዝርዝር ይፋ ሢያደርግ ኢትዮጵያንም ከዓለም 60ኛ ደረጃ መቀመጧን ገልጿል።
የ138 አገራት ወታደራዊ ጥንካሬን የመዘነ መሆኑን የጠቆመው ተቋሙ፤ በዓለም በወታደራዊ ኃይላቸው ኃያላን ተብለው በቀዳሚነት የተቀመጡት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ከአንድ አስከ ሥድሥተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።