ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በዜጎች ላይ እየደረሰ ላለው ጥቃት እና ማባሪያ ላጣው ግድያ በቀጥታና በተዘዋዋሪ እጃቸውን ያስገቡ የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች ላይ ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠየቀ፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ መተከል ዞን በተደጋጋሚ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ እና መፈናቀል አስመልክቶ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው ምክር ቤቱ ጥያቄውን ያቀረበው።
ጉዳዩን በተመለከተ የውሳኔ ሐሳቡን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የውጪ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች፣ እንዲሁም የፍትህ እና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ናቸው፡፡
ሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች፣ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን የግድያ ጥቃት በተመለከተ ከሚመለከታቸው ጋር ተነጋግረው እና መረጃዎችን አጥርተው ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ተሰጥቷቸው በነበረ የቤት ሥራ መሠረት ነው ዛሬ ለምክር ቤቱ ሪፖርት እና የውሳኔ ሐሳብ ያቀረቡት፡፡
በትግራይ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 2 በመጥቀስም፣ ችግሩ እየሰፋ በሄደ ጊዜ የአዋጁን የተፈፃሚነት ወሰን ማስፋት እንደሚቻል በማስታወስ፤ በመተከል ዞንም ችግሩን በመደበኛ ሕግ ለመቆጣጠር ካልተቻለና ከክልሉ አቅም በላይ ነው ተብሎ ከታመነበት በክልሉ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማስፋት፣ የፌደራል መንግሥት የጀመረውን ሕግ የማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።