ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ ሽብርና ሕገመንግሥታዊ አንደኛ ችሎት ዛሬ ማለዳ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሊቀበል ቀጠሮ ቢይዝም ሆን ብለው ውዝግብ ለመፍጠር በመጡት የጃዋር መሐመድ ቤተሰቦች እና የቅርብ ዘመዶቹ አለባበስ ምክንያት ችሎቱ ሊቋረጥ ችሏል።
የተከሳሾቹን የፍርድ ሂደት ለመከታተል ቢጫ ልብስ ለብሰው በፍርድ ቤት የተገኙ ሰዎች ወደ ፍርድ ቤቱ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ተከትሎ ተከሳሾች እና ጠበቆች ባሰሙት አቤቱታ መሠረት ነው ችሎቱ ሊቋረጥ የቻለው።
” ሰዎች ቢጫ ቀለም ያለው ልብስ በመልበሳቸው ወደ ፍርድ ቤት እንዳይገቡ መደረጉ አግባብ አይደለም፤ ቢጫ ልብስ በመልበሳቸው ብቻ ለእስር የተዳረጉ አሉ” ሲሉ ቅሬታቸውን ለፍርድ ቤት ያቀረቡት ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ እና ሐምዛ አዳነ (ቦረና) በዚህ ሁኔታ ቃላችንን መስጠት አንፈልግም ብለዋል።
ተከሳሾች በማረሚያ ቤት እና ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የሚለብሱትን ባለ ቢጫ ቀለም ቱታ በመልበስ አጋርነታችንን ለማሳየት ነው የመጣነው ያሉ የተለያዮ የጃዋር መሐመድ ቤተሰቦች፣ የቅርብ ዘመዶች እና ጥቂት ደጋፊዎች ፍርድ ቤቱ አካባቢ ግርግር ለመፍጠር መሞከራቸውን ተከትሎ በጸጥታ ኃይሎች ሲያዙ ለማየት ተችሏል።