ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ጀዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሐምዛ አዳነ እና አቶ ሸምሰዲን ጠሃ የረሃብ አድማ ማድረግ ከጀመሩ 6 ቀናት አልፏቸዋል ተባለ።
ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ያሉት እነ ጃዋር የርሃብ አድማ ላይ ለመሰንበት የተገደዱት የፖለቲከኞች እስር መበራከቱ እና በመገናኛ ብዙኃን የሚደርስባቸውን ጫና በመቃወም መሆኑ ተነግሯል።
ፖለቲከኞቹ እያደረጉት ያሉት የረሃብ አድማ አድክሟቸዋል ያሉት ጠበቃቸው ቱሊ ባይሳ፤ ደንበኞቻቸው ለማነጋገር በሄዱበት ወቅት ወጥተው ሊያነጋግሯቸው ስላልቻሉ ተኝተው ባሉበት ለማነጋገር ተገድጃለሁ የሚል አስገራሚ አስተያየት ሰጥተዋል።
ትናንት ደንበኞቻቸውን ሄደው ማነጋገራቸውን የሚያስረዱት አቶ ቱሊ፤ “የረሃብ አድማ ከጀመሩ ስድስተኛ ቀናቸው ነው። ከዚህ ቀደም ልንጠይቃቸው ስንሄድ መጠየቂያ ስፍራ ጋር መጥተው ነበር የሚያነጋግሩን። አሁን ግን ወደ እዛ እንኳን መጥተው ሊያነጋግሩን ስላልቻሉ በተኙበት ቦታ ሄደን ነው ያነጋገርናቸው። ድምጻቸውም፤ ሰውነታቸውም ተዳክሟል” ሲሉም ለቢቢሲ ሰጥተዋል።