ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በእስር ላይ የሚገኙት ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሐምዛ አዳነ እና ሸምሰዲን ጠሃ የረሃብ አድማ ማድረግ ከጀመሩ 11 ቀናት አልፏቸዋል ተባለ።
የኦሮሞ ብሔርተኛ ፖለቲከኞቹን ትናንት በረሃብ አድማ ውስጥ በቆዮበት አስራ አንደኛ ቀን ጎብኝቻቸዋለሁ በማለት ለቢቢሲ የተናገሩት ጠበቃቸው፤ እስረኞቹ በእጅጉ ተዳክመዋል ብለዋል።
አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ አብረው የታሠሩት ፖለቲከኞች አሁንም በረሃብ ላይ ናቸው ያሉት የአቶ በቀለ ገርባ ባለቤት ወ/ሮ ሀና ረጋሳ፤ ጤንነታቸው ያሳስበኛል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ከአራቱ ተከሳሾች በተጨማሪም የረሃብ አድማውን በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥር የሚገኙት የአቶ ጃዋር መሐመድ ጠባቂዎች እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋዜጠኛ መለሰ ዲሪብሳ ከተቀላቀሉ 6 ቀናት እንደሞላቸውም ተሰምቷል።
“አንዳንዶቹ በሰው ድጋፍ ነው ከክፍላቸው የሚወጡት። በተለየ ደግሞ ዘግይተው የረሃብ አድማውን የተቀላቀሉት በጣም ከብዷቸዋል” ያሉት ጠበቃ ሙለታ፤ እነ ጃዋር ምርመራ ሐኪሞቻቸው ካደረጉላቸው በኋላ ውሃ ካልወሰዱ አንዳንድ የሰውነት አካላቸው ሥራ ሊያቆም እንደሚችል ስለ ነገሯቸው በግድ ውሃ እየወሰዱ ያሉት። ምግብ የሚባል ነገር አፋቸው ጋር እየደረሰ አይደለም ሲሉም ተደምጠዋል።