ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር የአውሮፓ ሕብረት በትግራይ ክልል ከሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ጋር በተገናኘ ያወጣው መግለጫን ውድቅ አድርጓል።
መግለጫው በትግራይ ያለውን ተጨባጭ እውነታን ያላገናዘበ ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በክልሉ እያቀረበ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ ከግንዛቤ ያልከተተ ነውም ሲልም አጣጥሎታል።
የአውሮፓ ሕብረት ትናንት ባወጣው መግለጫ በትግራይ እየተፈጠረ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ እጅጉን አሳስቦኛል ማለቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢያዎች ክልከላ እንዳይደረግባቸው እና መንግሥት ለስደተኞችና ሲቪሎች ጥበቃ እንዲሰጥም ሕብረቱ ጠይቋል።
“መንግሥት በአካባቢው የሕግ ማስከበር ስራን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሕብረቱ የሚያወጣው መረጃ ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ እና ተገቢነት የሌለው ነው” ሲል ምላሽ የሰጠው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቱ በበርካታ የትግራይ ክልል ተደራሽ እንዲሆን መንግሥት እየሰራ ነው፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች እንዲጎበኝ ተደርጓልም ሲል አብራርቷል።