ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሙቀቱ መጠን እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በጋምቤላ ክልል የመንግሥት የሥራ ሰዐት ለውጥ ተደረገ።
የክልሉ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ፒተር ሆዎ፤ እንደገለጹት፣ የሙቀቱ መጠን እየጨመረ በመምጣቱና ለስራ አመቺ ባለመሆኑ ከየካቲት 3/2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ወራት የሚቆይ ጊዜያዊ የመንግሥት የሥራ ሰዐት ለውጥ መደረጉን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በመደበኛው የሥራ ሰዐት ከጠዋቱ አንድ ሰዐት እስከ ሥድሥት ሰዐት ተኩል ይሰጥ የነበረው አገልግሎት ከአንድ ሰዐት እስከ አምስት ሰዐት ተኩል እንዲሆን ተወስኗል። በተመሳሳይ ከሰዐት በኋላ ከዘጠኝ ሰዐት እስከ አስራ አንድ ሰዐት ተኩል የነበረው አገልግሎሎት አሰጣጥ ከዐሥር ሰዐት እስከ አስራ ሁለት ሰዐት ተኩል እንዲሆን መወሰኑን ሓላፊው አስረድተዋል።
የስራ ሰዐት ለውጡ ወይና ደጋ የሆነውን የማጃንግ ዞን አይጨምርም ያሉት ሓላፊው፤ የመንግሥት ሠራተኞች በተጠቀሰው ጊዜ ወደ ቢሮ በመግባት የተለመደውን ሥራቸውን እንዲያከናኑ አሳስበዋል።
በብሔራዊ ሜትሮዎሎጂ ኤጀንሲ የጋምቤላ ክልል አገልግሎት ማዕከል መረጃ ፤ በአሁኑ ወቅት የክልሉ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን 40 ነጥብ 4 ዲግሪ ሴልሽየስ፣ የሌሊቱ ደግሞ 16 ነጥብ 6 ዲግሪ ሴልሽየስ መሆኑን ይፋ አድርጓል።