ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በ24 ሰዐት ውስጥ አራት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገንዘብ እናባዛለን ያሉ ሁለት ካሜሮናውያን በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
በፓስፖርት ስማቸው ናዋ ሳምፕሰን እና ጁዲ አያምባንግ ተብለው የሚጠሩት እነዚህ ካሜሮናዊያን ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ ቆይታቸው ማርክ እና ሳምሶን በሚሉ ሃሰተኛ ስሞች እንደሚጠቀሙ የገለጸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፤ ተጠርጣሪዎቹ የደቡብ አፍሪካ ዜግነት ጭምር እንዳላቸው በመናገር እና ከተለያዩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ቢቆዮም አዲስ አበባ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ተቋም ጋር ባደረገው ክትትል እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ገልጿል።
ወንጀለኞቹ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋን በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኝ አንድ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ ቀጥረው በማግኘት፤ “2 ሚሊዮን ትክክለኛ የአሜሪካ ዶላር ገንዘብ ይዘህ ከመጣህ በ24 ሰዐት ውስጥ በሁለት እጥፍ በማተም በአጠቃላይ አራት ሚሊዮን ዶላር ስለሚሆን 40 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ላንተ ቀሪውን 60 በመቶ ገንዘብ ደግሞ ለራሳችን እንወስዳለን” ብለው እንዲስማማ በማግባባት የማታለል ወንጀል ሲፈጽሙ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።