ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የነዳጅ ጭማሪ ዋጋን ተከትሎ በአዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት መከሰቱን ኢትዮጵያ ነገ በተለያዮ አካባቢዎች ተዘዋውሮ መታዘብ ችሏል።
መንግሥት ፈጽሞ ሊቆጣጠረው ያልቻለው የኑሮ ውድነት ባለፉት አስራ ሁለት ወራት ውስጥ ተከስቶ የነበረ ቢሆንም ካሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ አንስቶ የታየው የዋጋ ጭማሪ ወደር የማይገኝለት መሆኑን ለመታዘብ ተችሏል።
ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ሩዝ፣ የስንዴ ዱቄት፣ ዘይት እና መሰል ሕዝቡ አብዝቶ የሚጠቀምባቸው የዕለት ተዕለት የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በሚያስደነግጥ መልኩ ወደ ላይ ንሯል። እንደ ልብ ማግኘትም አዳጋች ሆኗል።
የዳቦ ዋጋ ከሥድሥት እስከ አስራ ሁለት ብር አሻቅቧል። ደሃው የሕብረተሰብ ክፍል በአቅሙ አማራጮችን መጠቀም እንኳን እንዳይችል እንዳደረጉት ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸውልናል።
የህዝቡ ገቢ ከኑሮ ውድነቱ በተመጣጠነ መልኩ እያደገ አለመሆኑ እና መንግሥትም ምንም አይነት የደምዎዝ ጭማሪ በዚህ ወቅት አለማድረጉ የአዲስ አበባ ነዋሪ የጭንቅ ኑሮ እየገፋ ይገኛል።