ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በያዝነው ዓመት ይካሔዳል በተባለው ምርጫ ላይ ኦነግ እንደማይሳተፍ ተደርጎ የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ፓርቲው ገለጸ።
በወርሃ ግንቦት መጨረሻ እና ሰኔ ወር ላይ በሚካሄደው ምርጫ ይሳተፋሉ ተብለው ከሚጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው ኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በአሁኑ ወቅት ድርጅታቸው የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎች እየገጠሙት ቢሆንም በመጪው ምርጫ ላለመሳተፍ አለመወሰኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የዕጩዎች ምዝገባ ቀነ ገደብ እየተጠናቀቀ ነው። መንግሥት ደግሞ ጫና እያደረግብን ነው” ያሉት አቶ ዳውድ፤ “በምርጫው አንሳተፍም የሚል ውሳኔ ላይ ግን አልደረስንም” ብለዋል።
“ከምርጫው እራሳችንን አግልለናል ብለን አላወጅንም። ከእንዲህ አይነት ውሳኔ ለመድረስ የራሱ አካሄድ አለው። መወያየት ያለብን ነገር አለ” ያሉት የግንባሩ ሊቀ መንበር ኦነግ ከምርጫ ተወዳዳሪነት እንደወጣ ተደርጎ የቀረበው መረጃ ሐሰተኛ ነው ሲሉ አስተባብለዋል።