ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በበርካታ ማኅበራዊ ድረ-ገጾች ስለ ትግራይ ክልል የሚሰራጨው መረጃ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በትክክል አያሳይም ተባለ።
“የኤርትራን ወታደራዊ መለዮ ለብሰው የህዝቡን ንብረት የሚዘርፉትና ሴቶችን የሚደፍሩት የጁንታው ስርዓት የፈጠራቸው ወንበዴዎች እንጂ የኤርትራ ወታደሮች አይደሉም” ያሉት የሰሜናዊ ዞን ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሙሉ ብርሃን ሀቁን ሕዝብ ሊያውቀው ይገባል ብለዋል።
ህወሓት ባለፉት 46 ዓመታት የትግራይን ህዝብ ከኢትዮጵያዊነት ለመነጠል የሀሰት ትርክት እየደረሰ ከማወናበድ ውጭ ምንም ጥቅም እንዳላስገኘለት ህዝቡ ተገንዝቧል ያሉት የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራ አባል፤ “አክሱማዊያን ኢትዮጵያዊያን አልነበሩም’ የሚል የሀሰት ድርሰት ተዘጋጅቶ ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመነጠል የሚሞክር ቡድንም እንዳለ አስረድተዋል።
ይህ ቀኑ የጨለመበት ቡድን የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል ሀብት እየዘረፉ ፣ ሴቶችን እየደፈሩ ነው በሚል ፈጽሞ ከእውነት የራቀ መረጃ እያሰራጨ እንደሆነም ከመግለጫው መረዳት ተችሏል።