ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ አለመግባባቶችን መሰረት በማድረግ ለፍርድ ቤቶች የሚቀርቡ ቅሬታዎች የሚስተናገዱበት ሥነ-ሥርዓት ረቂቅ ደንብ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መቅረቡ ተሰማ።
በምርጫ አለመግባባቶች አፈታት ላይ ዳኞች ስላላቸው ኃላፊነት የምርጫ ሥርዓት ዙሪያ ያተኮረ ውይይት በዓለም ዐቀፍ ፋውንዴሽን (IFES)- የህግ አማካሪ በሆኑ ባለሙያ ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዓዋጅ ቁጥር 1162/2011 ድንጋጌዎችን ከምርጫ አለመግባባት አፈታት ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች እና መርሆዎች አኳያ የመተርጎም አስፈላጊነት ላይም ትንታኔ ተሰጥቶበታል።
ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምርጫ ጉዳይን አፋጣኝ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ እንዲቻል የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያደርግ መቆየቱንና በሶስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ችሎቶቹን የማደራጀትና ዳኛችን የመመደብ ሥራ ማካሄዱን ገልጿል።