ታላቁ “ዐቢይ ጾም” ተጀመረ!

ታላቁ “ዐቢይ ጾም” ተጀመረ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና አማኞች ዘንድ የተለየ መንፈሳዊ ትርጉም የሚሰጠው ታላቁ የ”ዐቢይ ጾም” ሰኞ መጋቢት 29/2013 ዓ.ም ተጀምሯል።

ሊቀ ጉባኤ ቀለመወርቅ ውብነህ የ”ዐቢይ ጾም”ን መጀመር አስመልክተው በሰጡት ትምህርት “ዐቢይ ጾም ጌታችን ከተጠመቀ በኋላ ዐርባ ቀን የጾመው፤ እኛም እንድንጾማቸው በቤተ ክርስቲያናችን ከታዘዝናቸው ሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት አንዱ ነው፡፡

ምእመናን ጌታችን ያደረገውን ምሳሌ ተከትለን ጾሙን በየዓመቱ እንጾመዋለን፡፡ ዐቢይ ጾም ስምንት ሳምንታት (፶፭ ቀኖች) አሉት፡፡ በውስጡ ስምንት ቅዳሜዎች፣ ሰባት እሑዶች ይገኛሉ፡፡ ይኸውም ዐሥራ አምስት ቀን ማለት ነው፡፡ እነዚህ ቀናት ከጥሉላት እንጂ ከእኽል ውኃ ስለማይጦሙ የጦሙ ወራት ዐርባ ቀን ብቻ ይኾናል” ብለዋል። “ጾም ማለት መተው መከልከል ማለት ነው” ሲሉ የገለፁት ጾም በእግዚአብሐር የተቀደሰ ተግባር ስለኾነ ወደ ቅድስና ጎዳና የሚመራ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችንም ሥርዓት ሠርታ ጾመን ከአምላካችን ጋር ኅብረት እንዲኖረን፤ መንፈሳዊ ኃይል እንድናገኝ ታደርጋለች፡፡ በጾም ወራት ከመባልዕት መከልከል ብቻ ሳይኾን ዐይን ክፉ ከማየት፣ አንደበት ክፉ ከመናገር፣ ጆሮ ክፉ ከመስማት መቆጠብ እንደሚገባው በቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፎአል፡፡

‹‹ይጹም ዐይን ይጹም ልሳን እዝንኒ ይጹም እምሰሚዓ ኀሡም በተፋቅሮ›› እንዲል ቅዱስ ያሬድ /ጾመ ድጓ/፡፡ በጾም ወራት ላምሮት፣ ለቅንጦት የሚበሉ ወይም ለመንፈሳዊ ኃይል ተቃራኒ የኾኑ ሥጋዊ ፍትወትን የሚያበረታቱ፣ ሥጋንና የሚያሰክሩ መጠጦችን /ዳን.፲፥፪-፫/፣ ቅቤና ወተትን ከመጠቀም መታቀብ እንደሚገባ ታዟል /መዝ.፻፰፥፳፬፣ ፩ቆሮ.፯፥፭፤ ፪ቆሮ.፮፥፮/፡፡” በማለትም መንፈሳዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

LEAVE A REPLY