ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ በትግራይ ክልል ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙት እነ አቶ ስብሀት ነጋ፣ ዶ/ር አብረሀም ተከስተ፣ አምባሳደር አባይ ወልዱ፣ አምባሳደር አባዲ ዘሙ፣ አቶ ቴዎድሮስ ሀጎስ፣ ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ፣ ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ፣ ሜ/ጀነራል ይርዳው ገብረ መድኅን፣ ሜ/ጀነራል ገብረ መድኅን ፍቃዱ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋን ጨምሮ በአጠቃላይ 21 ታሳሪዎች በጥሩ አካላዊ ደኅንነት ላይ አጠቃላይ ሁኔታውም ተቀባይነት ባለው መልኩ መያዛቸውን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እና የኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ በሚገኘው እስር ቤት የካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በመገኘት በታሳሪዎች አያያዝ ሁኔታ ላይ ክትትል ማድረጋቸውን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፣ በጉብኝቱም ታሳሪዎቹ በጥሩ አካላዊ ደኅንነት ላይ እንደሚገኙ፣ የሚገኙበት አካባቢና ክፍሎች ንፁህ እና ብዙም ያልተጨናነቁ፣ የተፈጥሮና የኤሌክትሪክ ብርሃን ያላቸው መሆኑንና አጠቃላይ ሁኔታው ተቀባይነት ያለው መሆኑን በመግለጫ አመልክቷል።