ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ሆሮጉድሩ ደንጉር ወረዳ ዳቢስ በሚባል ቦታ ኦነግ ሸኔ እና አባ ቶርቤ የተባሉት አማጺያን በአካባቢው በሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ በከፈቱት ጥቃት 29 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።
ጥቃቱ የደረሰው የዳቢስ ቀበሌ ነዋሪዎች ባላሰቡበት እና መደበኛ ሕይወታቸውን እየመሩ ባሉበት ወቅት ነው።
ታጣቂዎቹ በድንገት ግድያውን ከመፈፀማቸው በፊት፣ የአማራ ብሔር ተወላጆቹን ወደአንድ ቦታ ሰብስበው የሞባይል ስልካቸውን ከተቀበሉ በኋላ ጥቃቱን ማድረሳቸው ታውቋል።
ከሟቾቹ በተጨማሪ ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ ከ30 የማያንሱ ሰዎች ታግተው ወደ ጫካ መወሰዳቸው ተጠቁሟል።
በተመሳሳይ፣ በአማሮ ልዩ ወረዳ ዳኖ ቀበሌ በእርቅ ላይ የነበሩ ሰዎች መርሃ ግብራቸውን በፀሎት ሲጀምሩ የታጠቁ ኃይሎች መጥተው ኢሰብዓዊ ጭፍጨፋ ፈፅመውባቸዋል። በጥቃቱ ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ዜጎች ሞተዋል፤ ብዙዎችም ቁስለኛ ሆነዋል።