ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጣልቃ ገብነትን እና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን በመቃወም ሰልፍ እያካሄዱ ነው።
“አንድነት ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ትናንት በዋሽንግተን ዲሲ ሰልፉ የተካሄደ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም በኒውዮርክ ሌላ ሰልፍ የቀጠለ ሲሆን በአውሮፓ የመኖሩ ኢትዮጵያውያንም ተቃውሟቸውን በብራሰልስ ተቃውሟቸውን ማሰማት ጀምረዋል።
ሰልፈኞቹ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ የኢትዮጵያን ገፅታ ከማበላሸቱ ባሻገር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ዝቅ ያደረገ በመሆኑ እውነትን ለማውጣት እንደሚታገሉ አስታውቀዋል።
የዋሽንግተን ዲሲ ሰልፍ ተሳታፊዎች የተለያዩ መልዕክቶችን በመያዝ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተቃውሟቸውን ከማሰማታቸው ባሻገር፣ ሲ.ኤን.ኤንን ጨምሮ የውጭ አገር ሚዲያዎች የትግራይ ክልልን መልሶ ለመገንባት እና የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ የሚከናወነውን ተግባር እውቅና ሳይሰጡ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ላይ እንደሚገኙ በሰላማዊ ሰልፉ አስታውቀዋል።
የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኮንግረንስ አባላት ፊት ባቀረቡት ሪፖርት “በትግራይ ክልል ግድያዎችን ጨምሮ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ዩናይትድ ስቴትስ ተአማኒ መረጃ አላት። ሕዝቡ ከዚህ በኋላ የዘር ማጥፋትንም ሆነ የሰብአዊ መብትን የሚጥሱ የጸጥታ ኃይሎችን ማየት የለበትም።… ከኤርትራ ወታደሮች በተጨማሪ የአማራ ክልል ኃይሎችም ክልሉን ለቀው ይውጡ፣ በትግራይ ክልል የተፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ መደረግ አለበት” ማለታቸው ይታወሳል።