ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ዕድለኛው ክንዴ አስራት ይባላል፡፡ የዕድለኛዋ ልጁ ት/ቤት ክፍያ ደረሰኝ መጥፋት ለመቃጠል 2 ሳምንት የቀረውን የ20 ሚሊዮን 2013 እንቁጣጣሽ ሎተሪ 1ኛ ዕጣ አስገኝቶለታል፡፡
ክንዴ በተግባቢነቱና ችኩልነቱ ይታወቃል፡፡ በራሱ እውነት ነው ብሎ ላመነው ነገር ፍትለፊት ይጋፈጣል፡፡ በልጅነቱ ድቁና ተምሯል፡፡ ከቴክኒክና ሙያ ት/ቤትም ተመርቋል፡፡ በሞተረኛነት ሥራም ተሰማርቷል፡፡
የአርባምንጭ ከነማ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ማሕበር እንቅስቃሴ ውስጥ አይጠፋም፡፡
በቅርቡም ለሁለት ወራት አርባምንጭ ከነማ በድሬዳዋ በነበረው ቆይታ አብሯቸው ሰንብቶ ከጥሩ ውጤት ጋር ተመልሷል፡፡
ከሁሉም በላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአርባምንጭ ከተማ በጎ ፈቃደኞች ማህበር ጋር በመሆን በበጎ ፈቃድ ሥራ በአርባምንጭ ከተማ በስፋት እየተሳተፈ መልካም ነገርን አበርክቷል።
የእንቁጣጣሽ ሎተሪን ከአርባምንጭ፣ ከሻሸመኔ እና ከአዲስ አበባ እንደቆረጠ ይናገራል፡፡ የሎተሪ ማውጫውን ግን አላየም፡፡ በቅርቡ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የማፈላለጊያ ማስታወቂያ ማውጣቱን ያዬ ቢሆንም መቁረጡን አላስታወሰም፡፡ ከድሬዳዋ መልስ ግን ልጁ ከምትማርበት ት/ቤት ስልክ ተደወለለት፣ የልጅህ ወርሃዊ ክፍያ አልተከፈለም በሚል፡፡ እሱ ደግሞ መክፈሉን ለማረጋገጥ የከፈለበትን ደረሰኝ ሲያፈላልግ ሎተሪውን ያገኘዋል፡፡ ቁጥሩንም በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከተለጠፈው ጋር ሲያመሳክር ተመሳሳይ ሆኖ አገኘው፡፡ ጊዜ አላባከነም፣ የቀረው 1 ሳምንት ስለሆነ የትራንስፖርት ብር ተበድሮ ወደ አዲስ አበባ አቀና፡፡ በእጁ የነበረው የሎተሪ ቅጠል 3 (ሀ፣ለ፣ሐ) ስለሆነ 12 ሚሊዮን ብር ደረሰኝ ተቆረጠለት፡፡ 2ቱን ቅጠል ግን ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በቅርቡም 12 ሚሊዮን ብሩን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አርባምንጭ ከተማ በሚያዘጋጀው ፕሮግራም ይረከባል፡፡