በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባት ተጀመረ!

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባት ተጀመረ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በፌደራል ደረጃ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በኤካ ኮተቤ የኮቪድ ማእከል በመገኘት የክትባት መርሃግብሩን አስጀምረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዲላሂ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ በመገኘት ፕሮግራሙን ያስጀመሩ ሲሆን፣ ሚኒስትር ዴኤታ አለምጸሀይ ጳውሎስ በሀረር ከተማ በመገኘት   እንዲሁም የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የክልል ጤና ቢሮ ሃላፊዎች እና የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የክትባት መርሀግብሩን በይፋ አስጀምረዋል።

ክትባቱን ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት፤ የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች፣ እድሜያቸው ከ65 አመት እድሜ በላይ የሆኑና ተጓዳኝ ህመም ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን እንዲያገኙ ደረጃ በደረጃ ለመከተብ መርሀግብር ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ቀደም ሲል  የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ህብረተሰብን በማሳተፍ የተለያዩ መከላከያ ምክሮች እየተተገበሩ ሲሆን ነገር ግን በሚታየው ከፍተኛ መዘናጋት በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል።

ሁኔታው ተባባሶ ወደማንወጣው ደረጃ ከመድረሱ በፊት እንዲሁም ክትባት መገኘት ማለት ጥንቃቄን ማቆም ማለት እንዳልሆነ ተገንዝቦ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኝ ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የጤና ባለሙያዎች፣ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ማስክ ማድረግህ፣ የእጃቸውን ንጽህና በተደጋጋሚ መጠበቅና በየትኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ተገቢውን የጥንቃቄ መንገዶችን በመተግበር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያደርሰውን ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች በጋራ እንድንከላከል ሲልም የጤና ሚኒስትር አሳስቧል።

LEAVE A REPLY