ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ላለፉት ስድስት አመታት በተከታታይ ሲካሄድ ቆይቶ አምና በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው “ጉማ የፊልም ሽልማት”
የፊታችን መጋቢት 18 ቀን 2013ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል በሚደረግ ስነስርአት እንደሚካሄድ ተገለፀ።
አዘጋጆቹ ዛሬ በስካይላይት ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፣ በሰባተኛው የጉማ ፊልም ሽልማት በ2011 እና በ2012 ተሰርተው በሀገር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ ከቀረቡ ፊልሞች መካከል 45 ፊልሞች ተመዝግበው ለውድድር የቀረቡ ሲሆን፣ እጩ በመሆን ለመጨረሻ ዙር የቀረቡ ፊልሞችም የፊታችን ሀሙስ ይፋ ይደረጋሉ ተብሏል።
ውድድሩ የሚካሄደው በ18 ምድቦች (የሽልማት ዘርፎች) መሆኑን አያይዘው የገለፁት አዘጋጆቹ በዘንድሮው “7ኛው የጉማ ፊልም ሽልማት” የህይወት ዘመን ተሸላሚ በመሆን ክቡር ዶክተር ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) መመረጣቸውን አስታውቀዋል።