ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኮሮና ቫይረስ ስጋት ምክንያት ከኢትዮጵያ፣ ከኳታር፣ከኦማንና ከሶማሊያ ወደ ግዛቷ የሚገቡ ተጓዦች ላይ ከመጪው አርብ ጀምሮ እገዳ መጣሏን እንግሊዝ አስታወቀች።
ከዚህ ቀደም 30 አገራት ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳ የቆየችው እንግሊዝ አሁን አራቱን ሀገራት ያገደችው፣ የወረርሽኙ ክትባት ዘመቻ ወሳኝ ደረጃ ላይ ባለበት ወቅት በደቡብ አፍሪካ እና በብራዚል የተገኙትን የመሰሉ አዲስ አይነት የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎችን ለመከላከል ነው ተብሏል።
የእንግሊዝ መንግስት እገዳውን ይፋ ባደረገበት መግለጫ እንዳስታወቀው ከኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት አገራት ከመጋቢት 10/2013 ዓ.ም ቀደም ብሎ ካሉት 10 ቀናት ጀምሮ ጉዞ ያደረጉ ወይም በዚያ ያለፉ ሰዎች ወደ እንግሊዝ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም።
ተጓዦቹ የብሪታኒያ ወይም የአየርላንድ ዜጎች ወይም የረጅም ጊዜ ቪዛን ጨምሮ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ከሆኑ ግን እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል።