ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከእጮኛው ጋር ቀለበት ካሰረ ገና አንድ ወር ያልሞላው “የሙሽራው ቴዎድሮስ አበባው” ግድያ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ለከፍተኛ ቁጣ ከማነሳሳቱም ባሻገር የማህበራዊ ሚዲያው ዋነኛ አጀንዳ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ቡና የልብ ደጋፊ የሆነውና “ቴዲ ቡናማው” በሚል ስም የሚታወቀው ወጣቱ የራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ባለበት ምሽት ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በስለት ተወግቶ ነው ህይወቱ ያለፈው። አሳዛኙ የሞት ዜና ከተነገረ ጀምሮም በተለይ የአዲስ አበባ ወጣቶች ሀዘናቸውን በቁጣና ቁጭት እየገለፁ ይገኛሉ።
በወጣት ቴዎድሮስ አበባው ላይ የግድያ ወንጀል የፈፀሙ ተጠርጣሪዎችን ለማወቅና ለመያዝ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቆ በአጭር ቀናት ውጤቱን ለህዝብ እንደሚያሳውቅም ገልጿል፡፡
ወጣት ቴዎድሮስ አበባው መጋቢት 6 ቀን 2013 ዓ/ም በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ቤተል አዲስ ተስፋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በግምት ከምሽቱ 5 ሰዓት ገደማ ባልታወቁ ሰዎች በተፈፀመበት ወንጀል ህይወቱ አልፎ በመገኘቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።
በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ግለሰቦች ላይ ተመሳሳይ ወንጀሎች ተፈፅመው ፖሊስ ባደረገው ክትትል ፈፃሚዎቹን በአጭር ቀናት ውስጥ በቁጥጥር ስር አውሎ ለህዝብ ይፋ ማድረጉን ያስታወሰው ኮሚሽኑ በተለይም የግል ትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡ አሽከርካሪዎች እና ተሽከርካሪዎች ላይ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 8 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ በማጣራት ላይ እንደሚገኝ መጋቢት 07 ቀን 2013 ዓ/ም በኮሚሽኑ የፌስቡክ ገፅ መረጃ ማሰራጨቱን አመልክቷል፡፡
በቴዲ ገዳዮች ዙሪያ መንግስት ምርመራ እያደረገ መሆኑን እንዳረጋገጡ በሀዘኑ ቤት ለተገኘው ዘጋቢያችን የገለፁለት የሟቹ የቅርብ ጓደኞች በበኩላቸው “ቴዲ ቡናማው የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ሳለ ሶስት ሰዎች ናቸው ጥቃት ፈፅመው የገደሉት” ብለዋል።
ጓደኞቹ እንደሚሉት ቴዲ የራይድ ታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ገና አንድ ወር እንኳን ያልሞላው ሲሆን፣ ቴዲ በባህሪው ሁሌም በተጠራበት የሚገኝ፣ የታመሙ ወገኖችን ለማሳከም የሚሯሯጥ፣ ሰዎችን ለመርዳት ዘወትር የማይደክም እንደነበርና ይህ ልበ ብሩህ ወጣት የሰዎች ጭካኔ ሰለባ ሆኖ በግፍ መገደሉ የከተማዋን ወጣቶች ሊያስቆጣ ችሏል።
የቴዎድሮስ አበባው ስርዓተ ቀብር እጅግ በርካታ ቁጥር ያለው የከተማዋ ነዋሪ በተገኘበት ዛሬ 6:00 ሰዓት ላይ በቀራኒዮ ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ የተፈፀመ ሲሆን፣ በስርዓቱ ላይ የተገኙት መምህር ምህረተአብ “መግደል መሸነፍ ነው። የአድዋ ድል በዓል ላይ ‘ቢመችሽም ባይመችሽም ሸገር ፊንፊኔ አይሆንልሽም’ አለ ተብሎ በተጠና መልኩ በግፍ የተገደለው ደግ ወጣት ቴዎድሮስ አበባው ነፍስ ይማር! የሸገር ልጆች ከመቼውም በላይ አንድ ሆናችሁ የምትቆሙበት ጊዜ ደርሷል” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።