ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) በሀገሪቱ ፍትህና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በጥምረት ለመስራት ያስችላል ያሉትን የትብብር ስምምነት መፈራረማቸውን ዛሬ በሰጡት የጋራ መግለጫ ይፋ አድርገዋል።
ሁለቱ ፖርቲዎች በጋራ መግለጫቸው እንዳሉት ትብብሩ በቀጣይ በአገሪቱ እንዲፈጠርና እንዲጎለብት ለሚፈለገው የአገራዊ በጎ ሀይሎች ጥምረት መሠረት እንዲሆን የታለመ ነው።
የአሁኑ የጋራ ስምምነት በመጪው አገራዊ ምርጫ የመራጮችን የጋራ ፍላጎትና ራዕይ ለማሳካትና በጋራ ለመስራት በማሰብ የተመሰረተ የፖለቲካ ትብብር መሆኑን የገለፁት ፓርቲዎቹ፣ በአገሪቱም ሆነ በዜጎች ላይ የተጋረጡ ፈተናዎች መኖራቸውን አመልክተው “ይህንን ከመቼውም ጊዜ በላይ በትብብር ለመታገል በቁርጠኝነት እንሰራለን። ትብብሩ ከምርጫው በኋላም ይቀጥላል” በማለት አስታውቀዋል።