ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ “የአዲስ አበባ ፖሊስን የደንብ ልብስ የለበሱ ነገር ግን የፖሊስ መታወቂያ የሌላቸው ጸጉረ ልውጥ ወጣቶች በየቤቱ እየዞሩ ብሔር እና ሃይማኖት በመመዝገብ ላይ ናቸው” በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በተላለፈው ሃሰተኛ መረጃ ዙሪያ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
“እነዚህ ከየት እንደመጡ የማይታወቁ ጸጉረ ልውጦች በተወሰኑ ብሔሮችን እና ሃይማኖቶችን ለይተው ለማጥቃት እየተንቃሰቀሱ ነው የሚሉ እና በነዋሪው ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያሳድሩ ሃሰተኛ መረጃዎች በስፋት እየተሰራጩ መሆኑን ኮሚሽኑ ደርሶበታል” ሲል ፖሊስ።
“በፀረ ሠላም ሀይሎች አየተሠራጨ ያለው ሀሠተኛ መረጃ ህብረተሰብን ለማደናገጥ እና ለማሸበር እንዲሁም ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት እንዲሁም በህብረተሰቡ ላይ የፀጥታ ስጋት ለመፍጠር ሆን ተብሎ ታቅዶና ታስቦ እየተሰራጨ ያለ ሀሰተኛ መረጃ ነው” በማለት ገልፆ፣ ከተማዋ ላይ ሰላም እንደሌለ በማስመሰል ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት ላይ ክትትል በማድረግና በምርመራ በማጣራት በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራን እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።