በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለው “የእሳት ቃጠሎ አደጋ” አሳሳቢ ሆኗል!

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለው “የእሳት ቃጠሎ አደጋ” አሳሳቢ ሆኗል!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በያዝነው መጋቢት ወር ብቻ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ የሚገኘው ድንገተኛ “የእሳት ቃጠሎ አደጋ” እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተመልክቷል።

ከቀናት በፊት በአሰቦት ገዳም ዙሪያ የተነሳውን እሳት ዛሬም ድረስ መቆጣጠር ያልተቻለ ሲሆን፣ እሳቱ አቅጣጫውን እየቀያየረ ለቁጥጥር አዳጋች አዳጋች ሆኗል።

የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ ብርሃኑ፣ እሳቱ በሰው ኃይል ይጠፋል ብሎ ማሰብ የማይቻልበት ደረጃ መድረሱን ገልፀው “መንግሥት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ይገባዋል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

ጉዳዩን እየተከታተሉ ለህዝብ እያሳወቁ ከሚገኙት መካከል አንዱ የሆኑት መምህር ኤፍሬም ዘደብረወግ በበኩላቸው፣ የእሳት ቃጠሎ አደጋው ተባብሶ ከትናንት ምሽት ጀምሮ የገዳሙን ዙሪያ በመክበብ ወደ ገዳሙ እየገባ እንደሆነ አስታውቀዋል።
“በገዳሙ አራቱም አቅጣጫ እየተስፋፋ ያለው እሳት፣ ከመናኒያኑ መኖሪያና ከቤተክርስቲያኑ በ25 ሜትር ርቀት ላይ ደርሷል” ያሉት መምህር ኤፍሬም፣ ወጣቶች ከተለያየ የሀገሩቱ አካባቢ ብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዘው በመምጣት እሳቱን ለማጥፋት ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ቢሆንም እሳቱ በሰው ኃይል የሚጠፋ እንዳልሆነ ገልፀዋል።

በተመሳሳይ፣ በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ ጎፍጭማ ቀበሌ ልዩ ስሙ ታች አንባ በሚባል ቦታ የተከሰተ የእሳት ቃጠሎ፣ የእናትና ሦስት ልጆችን ህይወት መቅጠፉ ታውቋል።

“ወ/ሮ ሰገድ ይቴ የተባሉ ግለሰብ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ/ም ከሶስት ልጆቻቸው ጋር በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ከቀኑ 9.30 አካባቢ ለጊዜው መንስኤው ያልታወቀ ድንገትኛ እሳት ተነስቶ ቤቱ ተያይዟል” ያለው የምስራቅ ጎጃም ዞን ፓሊስ ጽ/ቤት፣ በወቅቱ ሟች ወ/ሮ ሰገድ ከቤቱ በራፍ ውጭ ላይ እንደነበሩ፣ እሳቱን አይተው ቤት ውስጥ ያሉ ልጆቻቸውን ለማውጣት እሮጠው በመግባት ሁለት ልጆችን አውጥተው ሶስተኛውን ከተወለደ 20 ቀን የሚሆነውን ህፃን ከተኛበት ለማንሳት ተመልሰው ወደቤት ሲገቡ የወጡት ሁለት ልጆች ተከትለዋቸው እንደገቡና ሁሉም ተመልሰው ሳይወጡ እንዳልወጡ ለማረጋገጥ መቻሉን አስታውቋል።
በሌላም በኩል፣ በስልጤ ዞን አልቾ ውሪሮ ወረዳ በትላንትናው እለት በቡኔ ቀበሌ በደረሰ ቃጠሎ 78 ቤቶች ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን፣ 450 ግለሰቦችም ቤት አልባ መሆናቸው ተገልጿል።
ለጊዜው የእሳት አደጋው መነሻ በውል ባይታወቅም፣ በአደጋው ከ57 ሚሊዮን 5መቶ ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ተጠቁሟል።

እንደዚሁ ሁሉ፣ በአንኮበር ወረዳ ወፍ ዋሻ ደን ላይ የተከሰተው የእሳት አደጋ አሁንም አለመቆሙ ተነግሯል። እሳቱን በሰው ሀይል ለመከላከል ጥረት ቢደረግም ማስቆም እንዳልተቻለ የወረዳው ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት 3:00 ሰዓት አካባቢ በአርባ ምንጭ ከተማ ሼቻ ገበያ ላይ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የእሳት አደጋ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።

አደጋው በአካባቢው ህብረተሰብ፣ በእሳት አደጋ መከላከል ብርጌድና በጸጥታ አካላት ጥረት በቁጥጥር ስር መዋሉን የገለፀው የከተማው ፖሊስ፣ በአደጋው የደረሰውን የጉዳት መጠንና መንስኤ እያጣራ መሆኑን አሳውቋል።

ከቀናት በፊት (መጋቢት 11/2013) በሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ላይ የእሳት ቃጠሎ አደጋ መከሰቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በፓርኩ የተከሰተው የእሳት ቃጠሎ አደጋ በሳሩ ላይ እና በአንዳንድ ዛፎች ላይ የተወሰነ ጉዳት ቢያደርስም ቃጠሎው ሳይሰፋ በኅብረተሰቡ እና በፓርኩ ሠራተኞች ከፍተኛ ርብርብ በቁጥጥር ስር መዋሉ ታውቋል።
በያዝነው መጋቢት ወር ብቻ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ይህን ያህል መጠን ያለው የእሳት ቃጠሎ አደጋ መድረሱ በቸልታ መታየት የሌለበት አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ያመለከቱ ወገኖች፣ መንግስት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊያጤነው እንደሚገባ አሳስበዋል።

 

LEAVE A REPLY