ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የደረሰውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ የመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) ሪፖርቱን ትላንት ሌሊት ይፋ አድርጓል።
ከበርካታ ሳምንታት ጥረት በኋላ የምርመራ ባለሞያዎቹን ወደ አክሱም ከተማ መላክ መቻሉን የገለፀው ኮሚሽኑ፣ ወደአካባቢው የተላኩ ባለሞያዎች ከየካቲት 20 እስከ የካቲት 26 ቀን 2013 ድረስ በከተማዋ በመቆየት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን፣ 45 የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የዓይን ምስክሮችን እና የሃይማኖት መሪዎችን ማነጋገራቸውን እንዲሁም 20 ሰዎች የተሳተፉበት የቡድን ውይይት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ማድረጋቸውን አመልክቷል።
በተጨማሪ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከአክሱም ቅድስት ማርያም ሆስፒታል፣ ከአክሱም ሪፈራል ሆስፒታል፣ ከሚመለከታቸው የቀበሌ መስተዳደር አካላት እንዲሁም ከሃይማኖት ተቋማት አገልጋዮች የተለያዩ የምስል፣ የድምጽ እና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን የገለፀው የኢሰመኮ ሪፖርት፣ በዚህ ምርመራው ያሰባሰባቸው መረጃዎች በተለይ ከኅዳር 19 እስከ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በነበሩት ሁለት ቀናት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደተፈፀመ አረጋግጧል።
የአክሱም ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች፣ ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ጦርነት ሸሽተው በከተማዋ የተጠለሉ ተፈናቃዮች እና የኅዳር ፅዮን ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ለማክበር ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ሰዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከአንድ መቶ በላይ ሲቪል ሰዎች በወቅቱ በአክሱም ከተማ በነበሩ የኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውንም ሪፖርቱ ያመለክታል።