ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለተማሩባቸው ሁለት ትምህርት ቤቶች 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉ ጥያቄ አስነስቷል።
በአፍሪካ ቀዳሚና በአለም ስመጥር የሆነው ዩኒቨርሲቲው ጠ/ሚኒስትሩ የተማሩባቸውን ት/ቤቶች ብቻ ለይቶ ድጋፍ ማድረጎ ነው “ለምን?” በሚል መነጋገሪያ የሆነው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ የተደረገላቸው ትምህርት ቤቶች የበሻሻ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና አጋሮ 2ኛ ደረጃ ትምርት ቤት ሲሆኑ፣ ዩኒቨርሲቲው 30 ዴስክቶፕ ኮምፒውተር፣ 13 ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ 200 ጠረጴዛና 75 ወንበር እንዲሁም አንድ መኪና ለወረዳው ትምህርት ፅህፈት ቤት ድጋፍ አድርጓል።
ለሴት ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ ሞዴስ፣ እንዲሁም ሳኒታይዘር፣ ሳሙና እና ደብተር ለትምህርት ቤቶቹ ድጋፍ ተደርጓል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና ድጋፉ መምህራንና ተማሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች በማቃለል ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ያግዛል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ተምረው ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሳቸውና የሰላም የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው ለበርካቶች መነቃቃትን የፈጠረ በመሆኑ ትምህርት ቤቶቹ ለድጋፉ መመረጣቸውንም ተናግረዋል።
ይሁንና፣ የዩኒቨርሲቲውን ድጋፍ ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ በርከት ያሉ ዜጎች ሀሳብና ጥያቄዎችን እየሰነዘሩ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል “ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የአንድነትና እንጦጦ ፓርኮችን በቢሊዮን ብሮች እንዳሰሩ ይታወቃል። ለበሻሻና አጋሮ ትምህርት ቤቶቻቸውም ራሳቸው እንደማያንሱ እየታወቀ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጀት መድቦ የጠቅላዬን ት/ቤት ካልደገፍኩ ማለቱ ውሀ አያነሳም። የሚል መከራከሪያ አቀርበዋል። ይህ ደግሞ ከዚህ ቀደም ለነበሩ መሪዎችም ሆነ ከአሁን በኋላ ለሚመጡ መሪዎች ተግባራዊነቱ ምን ድረስ ይሆናል የሚ ል ጥያቄ አስነስቷል።
ሌላ አስተያየት ሰጭ ደግሞ “ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለተማሩበት ትምህርት ቤት በራሳቸው መሪነት ከበቂ በላይ ማድረግ ይችላሉ። ይህን ማድረግ ግዴታቸውም ነው። የተማሩበትና የወከሉት አካባቢም ነው። አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አፍንጫው ስር ስንት የሚረዳ ትምህርት ቤት እያለ በሻሻ ምን አስኬደው?” ሲሉ ጠይቀዋል።