ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከዚህ ቀደም በተለያዩ አዋጆች ተበታትነው ስራ ላይ የነበሩ ንግድና ከንግድ ጋር የተያያዙ ህጎች ከተለያዩ ማሻሻያዎች ጋር በአንድ ተሰባስበው በአዲስ መልክ ተዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ረቂቅ ዛሬ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባካሄደው 12ኛ መደበኛ ስብሰባው ቀርቦ በሙሉ ድምጽ ፀድቋል።
ህጉን ለማፅደቅ የሚያስችለውን የውሳኔ ሐሳብ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ መሰረት አባተ እንዳሉት አዲሱ የንግድ ህግ ከአለም የንግድ ህጎችና አሰራሮች ጋር እንዲጣጣም ተደርጓል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገች ላለችው ጥረትና እንቅፋት የነበሩ ድንጋጌዎች ከህጉ እንዲፋቁ መደረጉም ተነግሯል፡፡
የቀደመው የንግድ ህግ በ1952 ዓ/ም ስራ ላይ ከዋለ በኋላ ለንግድ እንቅስቃሴው መቀላጠፍና ለአፈፃፀም አመቺ እንዲሆን ያስችላሉ የተባሉ ጥናቶች ላለፉት 34 አመታት ሲካሄድ የቆየ መሆኑንም ወ/ሮ መሰረት አስታውሰዋል፡፡
ህጋዊ ሰውነት ያላቸው የአስተዳደር አካላትና የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የህብረት ስራ ማህበራት በሽርክና የንግድ ማህበራት ውስጥ ባለድርሻ ሆነው ቢሳተፉ እንደ ነጋዴ ተቆጥረው ህጉ በእነዚህም ላይ የሚሰራ እንዲሆን መደንገጉንም ተናግረዋል፡፡
አዲሱና የንግድ ህግ ኢትዮጵያን ለንግድ ህግ ምቹ እንድትሆን ያደርጋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡