ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ትላንት ከሰአት በኋላ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ አስመራ ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከኤርትራው ፕሬዝዳት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ባደረጉት ውይይት “ድንበር ሲጠብቅ የነበረው የኢትዮጵያ ጦር በህወሓት መጠቃቱን ተከትሎ የኤርትራ ጦር ይዞ ከቆየባቸው የትግራይ መሬቶች ለቆ ለመውጣት ከስምምነት መደረሱን” አስታወቁ።
በዛሬው ይፋዊ መግለጫቸው “የሕወሓት ጽንፈኛ ቡድን ወደ ባህርዳር፣ ጎንደርና አሰመራ ሮኬት መተኮሱን” ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ድንበር ጠባቂው የሰሜን ዕዝ ጦር ድንገት በተከፈተበት ጥቃት መበታተኑና ወደአስመራ ሮኬት መወንጨፉ በኤርትራ ላይ የደህንነት ስጋት ማሳደሩን ተከትሎ ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበርም የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው መግባታቸውን ገልጸዋል።
“አስመራ ተገኝቼ ከኘሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ባደረግነው ውይይት የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ ግዛት ሙሉ በሙሉ ለቆ እንዲወጣና በኤርትራ ጦር ተይዞ የነበረውን ድንበር የኢትዮጵያ ሠራዊት በፍጥነት ተሰማርቶ እንዲጠብቅ ከስምምነት ደርሰናል” ሲሉ አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤርትራ ጦር ሱዳን እና ኢትዮጵያ በሚወዛገቡበት የአል-ፋሽጋ አካባቢ መስፈሩን የሚገልፅ ሪፖርት ያወጣ ሲሆን፣ የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚ/ር አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ስለተባለው ጉዳይ መረጃው እንደሌላቸው አመልክተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ አውጥቶ በነበረው ሪፖርት የኤርትራ ጦር በአል-ፋሽቃ ትሪያንግል መስፈሩን እንደደረሰበት ገልጿል።