ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የእንግሊዝ ፓርላማ ኢትዮጵያንና ኤርትራን በሚመለከት ክርክር ማድረጉ ሲታወቅ፣ ፓርላማው የተሰየመው የእንግሊዝ መንግስት ማዕቀብ እንዲጥል ውሳኔ ለማሰጠት ነበር ተብሏል።
ከትናንት በስቲያ መጋቢት 15/2013 በተካሄደው የፓርላማው የክርክር መድረክ፣ በትግራይ ተፈፅመዋል ስለተባሉ ግድያና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሔለን ሃየስ የተባሉ የፓርላማ አባል ባቀረቡት አራት ገፅ አቤቱታ የእንግሊዝ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን እርዳታዎች ሙሉ በሙሉ እንዲያቆም ተማፅነዋል::
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግስታት ላይ ጫና እንዲያሳድር መንግስታቸውን ለምነዋል::
እንደዚሁም፣ የእንግሊዝ ፓርላማ አባልና የመካከለኛው ምስራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት ጄምስ ክሌቨርሊ፣ በሴትየዋ የቀረበው ሃተታ ተገቢነት ያለውና ጉዳዩም አሳሳቢ መሆኑን፣ የእንግሊዝ መንግስትም ጉዳዩን እየተከታተለ እና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት እየተነጋገረና እየሰራ መሆኑን ገልፀው፣ ከትግራይ ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች በሩን ክፍት ማድረጉን አድንቀዋል።
“የእንግሊዝ መንግስት ለኢትዮጵያ ሰፊ ድጋፍ የሚያደርግ አጋር ነው። ለትግራይ ችግርም ከ15 ሚሊየን ፓውንድ በላይ ሰጥቷል። አሁንም ለተቸገሩ ሰዎች እርዳታውን ተደራሽ ለማድረግ ቅድሚያ ሰጥቶ በጥብቅ እየሰራ ይገኛል” ያሉት ጄምስ ክሌቨርሊ፣ የእንግሊዝ መንግስት በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ላይ ማዕቀብ እንደማይጥል አረጋግጠው “በመጭው ምርጫ ላይ ብዙ ስራ ይጠብቀናል።
እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጋር ትብብሯን ትቀጥላለች” በማለት በፓርላማው የቀረበውን ልመናና ተማፅኖ ውድቅ ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል።