ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በተለያዩ ምርጫ ጣቢያዎች በመከናወን ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በተያያዘ፣ በ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ለሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙሃን የምርጫ ቅስቀሳ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል ይፋ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከብሮድካስት ባለስልጣን ጋር በመተባበር ”በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምና ድልድል መመሪያ” እንዲሁም ”የመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የስነ-ምግባርና የአሰራር መመሪያ” ዙሪያ ትናንት ውይይት ያደረገ ሲሆን፣ በምርጫው ለሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙሃን የምርጫ ቅስቀሳ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል ዛሬ በብሮድካስት ባለስልጣን በኩል ይፋ ተደርጓል።
በዚህም 700 የሬዲዮ ሰዓት፣ 400 የቴሌቪዥን ሰዓት እና 600 የጋዜጣ አምድ ድልድል መደረጉ ተገልጿል።
በድልድሉ መሰረት 25 በመቶ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የሚከፋፈል ሲሆን 40 በመቶ ባቀረቡት የእጩዎች ብዛት መሰረት ይሆናል።
እንዲሁም 20 በመቶ ለሴት እጩዎች፣ 10 በመቶ ለአካል ጉዳተኞችና 5 በመቶ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም በነበረው ምርጫ በምክር ቤት በነበራቸው የመቀመጫ ብዛት መሆኑ ተጠቁሟል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተደለደለላቸውን የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ከዚህ ወር መጨረሻ ጀምሮ እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም የሚጠቀሙበት እንደሆነም ተገልጿል።
በእያንዳንዱ ሚዲያ የተመደበ ሰዓት የመንግስት ሬዲዮ ከሰኞ እስከ አርብ ቀንና ማታ 30፣ 30 ደቂቃ በሳምንት 300 ደቂቃ የሚጠቀሙበት እንደሆነ የገለፀው ብሮድካስት ባለስልጣን “የመንግስት ወይም የህዝብ ቴሌቪዥን የሚባሉት ኢቲቪ፣ ኦቢኤን፣ አማራ ቲቪ፣ ደቡብና አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከሰኞ እስከ አርብ ቀንና ማታ ለ30 ደቂቃ በሳምንት 300 ደቂቃ አገልግሎቱን ይሰጣሉ” ብሏል።
ሌሎች የክልል ሚዲያዎች ከሰኞ እስከ አርብ ዘወትር ማታ ማታ 30 ደቂቃ በሳምንት 150 ደቂቃ፤ የንግድ ቴሌቪዠን በሳምንት 2 ቀን ዘወትር ማታ ማታ ለ30 ደቂቃ በሳምንት 60 ደቂቃ እንደሆነና የአየር ሰአትና አምድ ድልድሉ የተደረገው በ60 ሚዲያዎች ላይ መሆኑም ተጠቁሟል።