ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ ስር ከነበሩት ክፍለ ከተሞች ተጨማሪ እንዲሆን ተብሎ ከወራት በፊት በአዲስ መልክ የተዋቀረው 11ኛው ክፍለ ከተማ “ለሚ ኩራ” ዛሬ መደበኛ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ታወቀ።
ትናንት ክፍለ ከተማው በይፋ ስራ መጀመሩን ለማብሰር ተብሎ በተሰናዳው ኘሮግራም ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ “አዲሱ ክፍለ ከተማ የለውጡ ትሩፋት ነው” ያሉ ሲሆን፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ የከተማ አስተዳደሩ ፖሊሲዎችን በመንደፍ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ እና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን የመመለስ ስራ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከቦሌ እና የካ ክፍለ ከተሞች 6 ነባር ወረዳዎች እና 4 አዳዲስ ወረዳዎችን በማደራጀት የአካባቢውን ነዋሪዎች እና አርሶ አደሮች የተለያዩ አገልግሎት እንደሚሰጥ ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።