ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– 6ኛውን አገራዊ የምርጫ ሒደት ተከትሎ የሚነሱ የምርጫ ክርክር ጉዳዮች በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱባቸው ፍርድ ቤቶች እየተደራጁ መሆኑ ተገለጸ።
የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ አቶ ተስፋዬ ንዋይ፣ በአገሪቷ ምርጫን በበላይነት የሚመራው ይሄው ፍርድ ቤት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚሰጣቸውን ውሳኔዎች መነሻ በማድረግ ቅሬታዎችን ለፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚቻል በአዋጅ መደንገጉን ገልጸዋል።
በተያያዘ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምርጫን ከመታዘብ በዘለለ ግጭት እንዳይከሰት መስራት እንዳለባቸው የተነገረ ሲሆን፣ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫን ለመታዘብ 155 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተመዝግበው 36 ድርጅቶች በ1ኛ ዙር ፈቃድ ማግኘታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አዘጋጅነት የሚካሄደው “አዲስ ወግ” የውይይት መድረክ የሩብ ዓመት ኘሮግራሙን ‘ሰላምና ደህንነት በምርጫ ወቅት’ በተሰኘ ርዕስ ዛሬ ተጀምሯል።
የውይይት መድረኩ በሦስት ክፍል እንደሚካሄድና የዛሬው መድረክም “የሰላማዊ ምርጫ መገለጫዎች እና መስፈርቶች” የሚል ርዕስ እንዳለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገለጿል። በጋዜጠኛ በጥበቡ በለጠ የአሀዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ኃላፊ አወያይነት፣ በሕይወት አለማየሁ የአንድምታ ኢቲ ሲቪል ዲስኮርስ መስራች እና በሕግ ባለሙያው ዶ/ር መሰንበት አሰፋ ተወያይነት መካሄዱንም ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል።
በዚሁ መድረክ ተሳታፊ ሆነው የተገኙት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ “መጪው ምርጫ ዕድልና ችግሮችን ይዟል። ሁለቱንም ተገንዝቦ ለመምረጥ የሚነሳና የሚመርጠውን አካል ሕጋዊነት ያረጋገጠ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ይህን መሰል ውይይቶች ያስፈልጋሉ። አጋጣሚውን ሁከት መቆስቆሻ ለማድረግ የሚፈልጉ ቅጥረኞችም አሉ ብለዋል።
አክለውም ችግሮችን ፈርተው ምርጫ አሁን አይኑር የሚሉም አካላት አሉ። የእኛ ዓላማ ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ ነውና ሁላችን ኢትዮጵያውያን ለዚያ እንተባበር። በመጪው ምርጫ የከተማዎች ሰላማዊነት አያሳስብም። ሊተኮርበት የሚገባው ሰው ወጥቶ ለመምረጥ ሕዝብ ደህንነት እንዳይሰማው የሚያደርጉ ቅጥረኞች ጉዳይ ነው። ይህንንም በጊዜ ለጸጥታ አካላት መረጃ በመስጠት ለመከላከል እንችላለን። በዚህ ምርጫ ካለፉት የተሻለ ውጤት ይገኛል ብዬ አምናለሁ” ሲሉ መናገራቸውንም ለማወቅ ተችሏል።