የግብጹ አል ሲሲ “በግድቡ ሳቢያ ሊገመት የማይችል አለመረጋጋት ሊፈጠር ይችላል” ማለታቸው ተነገረ!

የግብጹ አል ሲሲ “በግድቡ ሳቢያ ሊገመት የማይችል አለመረጋጋት ሊፈጠር ይችላል” ማለታቸው ተነገረ!

 4 የአረብ ሃገራት ግብጽን ደግፈው መግለጫ አወጡ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናኢትዮጵያ የውኃ ሀብቷን መጠቀም መብቷ እንደሆነና ታላቁ ሕዳሴ ግድብም “በሌሎች ላይ ይህ ነው የሚባል ችግር እንደማያመጣ” በተደጋጋሚ ስትገልፅ ብትቆይም የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ግን የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ተጠይቀው “የግብጽን ጠብታ ውኃ ማንም እንዲወስድ አይፈቀድለትም።… በግድቡ ሳቢያ በቀጠናው ሊገመት የማይችል አለመረጋጋት ሊፈጠር ይችላል” ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን አጃንስ ፍራንስ ኘሬስ ዘግቧል።

በሌላ በኩል፣ 4 የአረብ ሃገራት በግድቡ ጉዳይ ግብጽን ደግፈው መግለጫ ማውጣታቸው የተሰማ ሲሆን፣ ሃገራቱ በመግለጫዎቻቸው፣ ከግብጽ እና ሱዳን ብሔራዊ እና የውሃ ደህንነት መጠበቅ እንዲሁም ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያላቸውን አረባዊ አጋርነት ማሳወቃቸውንም ለመረዳት ተችሏል፡፡

የታችኞቹን የናይል ተፋሰስ ሃገራት ደግፋ ቀድማ መግለጫ ያወጣችው ሳዑዲ አረቢያ በመንግስቷ መገናኛ ብዙሃን በኩል “የግብጽ የውሃ ደህንነት ጉዳይ የመላው አረብ ብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው” የሚል አቋሟን አሳውቃለች። የሃገሪቱ ዜና አገልግሎት ዛሬ ሳዑዲ በዚሁ መግለጫዋ “የግድቡ ጉዳይ የሁሉንም ፍላጎት ባማከለ መልኩ መቋጫ እንዲያገኝ ለማድረግ ለሚደረጉ ጥረቶች ድጋፍ አደርጋለሁ” ብላለች።

የሳዑዲ አረቢያን መግለጫ ተከትለው ተመሳሳይ አቋማቸውን ያሳወቁት ደግሞ ኦማን፣ የመንና ባህሬን ሲሆኑ፣ እነርሱም በተመሳሳይ “የግብጽ የውሃ ደህንነት ጉዳይ የመላው አረብ ብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው” በማለት ጉዳዩን ከሁለቱ ሀገራት በላይ የመላው አረባዊያን ለማድረግ መፈለጋቸውን የሚያንፀባርቅ መግለጫ አውጥተዋል።

የአልሲሲን ንግግርና የአራቱ አረብ አገራትን መግለጫ በሚመለከት በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን በይፋ የተሰጠ መግለጫም ሆነ ማብራሪያ የለም።

LEAVE A REPLY