– የክልሉን መንግስት ተጠያቂ የሚያደርጉ ተበራክተዋል!
– ጠ/ሚ/ሩን ጨምሮ በርካቶች እያወገዙት ነው!
ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኦሮሚያ ክልል በምእራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ ቦኔ ቀበሌ፣ ከትናንት በስቲያ ምሽት በኦነግ ሸኔ የተፈፀመው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ከፍተኛ ቁጣ አስነስቷል።
ዛሬ በርካታ ዜጎች በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ሀዘንና ቁጭት አዘል አቋማቸውን ሲገልፁ የዋሉ ሲሆን፣ ብዙዎቹም እልህና ቁጣና አዘል መሆናቸውን መታዘብ ይቻላል።
“ላለፉት 30 ዓመታት በአማራው እየተፈፀመ የቀጠለው ግፍ በህይወት፣ በንብረት፣ በስነልቦና ያደረሰበት ጉዳት በወጉ አልተጠናም ፣ አልተደራጀም። በግለሰብ ደረጃ ተነግረው የማያልቁ ግፎች ከ1983 እስከዛሬ ድረስ አሉ” በማለት በግድያው የተሰማቸውን ሀዘንና ቁጭት የገለፀው ጋዜጠኛ አንሙት አብረሃም፣ “ሰው ያላጣው አማራ ይሕ ሁሉ ሲፈፀምበት ቆም ብሎ እየደረሰበት ያለውን የሚመለከትና በቃ የሚል ሳይኖር ዛሬም ቀጥሏል። …አማራው የሚደርስበትን ግፍ ተደራጅቶ ለመከላከል የሚያስችል ብቁ የፖለቲካ ኃይል አለመኖር ዛሬም ድረስ ያለ ችግር ነው።
ዛሬ ይህንን በወጉ ተረድቶ ለመፍትሔ የሚተጋ ዲያስፖራ፣ ምሁር፣ ባለሀብት፣ የፖለቲካ ኃይል የግድ ነው። ሀዘንና በደል በእያንዳንዱ አማራ ደጅ ደርሷል፤ እያንዳንዱ አማራም ቀኑን የሚጠብቅ ሆኗል” ብሏል።
ኡስታዝ አህመዲን ጀበል በበኩሉ፣ “በመላው ኢትዮጵያ በፖለቲካ ሸፍጥ ህይወታችሁን ያጣችሁ ንጹሐን ወገኖቼ አላህ ሀቃችሁን ያውጣላችሁ። የሰው ልጅ ሕይወት የረከሰበት ጊዜ ላይ ደረስን” በማለት የተናገሩ ሲሆን፣ የህግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላትም “ሀዘንን መግለጫ ቃላትም ይጠፋል። ወለጋ የአማራ ኦሽዊትዝ። የአማራ መታረጃ ቄራ” ሲሉ በስሜት የተሞላ ሀዘንና ቁጣቸውን ገልፀዋል።
“በኦሮሚያ ክልል በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች የቀጠለው አማራ ተኮር የዘር ማጽዳት በዓለም አቀፍ ወንጀል የሚያስጠይቅ ነው” በማለት ደግሞ የአማራ ምሁራን መማክርት መግለጫ አውጥቷል።
“የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የፌደራል መንግስት በአማራ ሕዝብ ላይ በአማፂ ኃይሎችና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በመሸጉ የሽብር ተኮር ተግባር ተባባሪ አካላት የጋራ ቅንጅት እየተፈፀመ ያለውን አማራን የማጥፋት ዘመቻ በቁርጠኝነት ባለመከላከላቸው እና የዘር ማጽዳት ወንጀሉን በአደጋው ልክ ባለማውገዛቸው በኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎች በአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል” ያለው የምሁራን መማክርቱ መግለጫ፣
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ የሚኖሩ ዜጎችን መሠረታዊ ደኅንነት የማስጠበቅ ሕጉ መንግሥታዊ ግዴታ ቢኖርበትም ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ካለመቻሉም በላይ ድክመቱን በኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ውስጥ ለመሽፋፈን መሞከሩ እንዳሳዘነው ገልጿል። እየተፈፀመ ያለውን አማራ ተኮር እልቂት የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው የክልሉ መንግስትና ሚዲያው መሽፋፈንን እንደ ስልት መከተል መምረጣቸው ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ሲል ድርጊቱን ኮንኗል።
“በፈዴራሉ መንግሥት በኩል እየተወስዱ ያሉ የፖለቲካና የሕግ አግባብ እርምጃዎች የማያባራውን እልቂት የሚመጥኑ አይደለም ያለው መማክርቱ የመንግሥት ሆደ ሰፊነትም ሆነ ታጋሽነት በዜጎች መቃብር ላይ በመቆም የሚገለጽ አይደለም፡፡ የዜጎቹን ሞት እንደዋዛ የሚያልፍና የሚመለከት መንግሥት ኃላፊነቱን ለመወጣት ቁርጠኝነቱ እና ፍላጎቱ የሌለው መንግስት እንጂ ዲሞክራሲን እየተለማመደ ያለ መንግስት አይደለም። ስለሆነም የፌደራሉ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ዜጎቹን ደኅንነት የማረጋገጥ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ብሏል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ያለው መማክርቱ የሕዝብ አብሮነትንና እሴቶችን የሚሸረሽሩ መግለጫዎችን ከማውጣትና ከከፍተኛ አመራር የማይጠበቁ ተንኳሽ ንግግሮች ከማሰማት ተቆጥቦ በክልሉ የሚኖሩ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጎች ከጥቃት እንዲከላከል ሲልም መማክርቱ ጠይቋል፡፡
የአማራ ብልጽግና ከፍተኛ አመራርና የገቢዎች ሚኒስትር የሆኑት የአቶ ላቀ አያሌው
“…ዛሬም ሌላ ልብን የሚያደማና በእጅጉ የሚያሳዝን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል። ድርጊቱም በምንም ሚዛንና መስፈርት ተቀባይነት የሌለው አሳፋሪና በታሪክ የሚያስጠይቅ ተግባር ነው:: ከአሁን በፊት በወያኔና ተላላኪዎች ሲፈፀም እንደነበር ግልፅ ነው:: ነገር ግን ዛሬ ላይ የሚልኩትና ስምሪት ሰጭውን አካል የደመሰሰ መንግስት እንዴት የተላላኪው አለቃ ሁኖ የዜጎችን ህይወት እየቀጠፈ ከአቅሙ በላይ ሊሆን ቻለ?? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ተገቢነት አለው ብዬ አምናለሁ” በማለት ተናግረዋል።
“…ይህ ድርጊት በአስቸኳይ ይቆም ዘንድ ወንጀለኞቹና ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ ተቋማትና ሀላፊዎች ወደ ፍርድ አደባባይ መቅረብ አለባቸው። ሁላችንም የተሰጠንን የህዝብ ሀላፊነት ካልተወጣን በህግ መጠየቅ አለብን። ይህ ካልሆነ የጅምላ ፍረጃ፣ የጅምላ ውንጀላና ክስ በሌላ በኩልም የጅምላ ከንቱ ውዳሴና ገፅታ ግንባታ እንዲሁም በተግባር የተሠራ ሥራን ከመቁጠር ይልቅ የተነገረን አጉል የተስፋ ቃል መቁጠር በሀገራችን በእጅጉ ጎልቶ እየታየ መጥቷል” ያሉት አቶ ላቀ አያሌው፣ “…ሁላችንም የዜጎችን ህይወት የእኔ ህይወትና የእኔ ቤተሰብ ናቸው ብለን አስበን ሃላፊነታችን ልንወጣ ይገባል ። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሁላችንም የስራችንን ማግኘታችን አይቀርም።
ስለዚህ ሰው የሆነ ሁሉ በሰው ህይወት ላይ መጨከን የለበትም:: ለተጎጂ ቤተሰቦች እና ለመላው ህዝባችን መፅናናትን እመኛለሁ” ሲሉ ሀዘንና ቁጭታቸውን ገልፀዋል።
በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በሰጡት መግለጫ “በኦሮሚያ ክልል በምእራብ ወለጋ ዞን በንጹሐን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት እናወግዛለን፡፡ የተሰማንን ጥልቅ ኀዘን ለሟች ቤተሰቦችና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ እንገልጻለን፡፡
ዓለማችን በወረርሽኝ ተጨንቃ መፍትሔ በምትፈልግበት በዚህ ሰዓት፣ ሆን ብለው በሰዎች ላይ መከራና ስቃይ የሚጨምሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች በምንፈልጋት ኢትዮጵያ ውስጥ ስፍራ የላቸውም። ጠላቶቻችን በውስጥና በውጭ ተደራጅተው ንጽሐን ዜጎቻችንን በመግደል የጀመርነውን ጉዞ ለማሸማቀቅና ከመንገዳችን ለማስወጣት ጥረት እያደረጉ ነው።
መሥዋዕትነት እየከፈልንም ቢሆን የኢትዮጵያን አንድነት አጠናክረን ጉዟችንን እንቀጥላለን። በሁሉም ቦታ በደርሰው ጥቃት አጸፋ እርምጃ በክልልና በፈዴራል መንግሥት ቅንጅት እየተወሰደ ይገኛል። በለዋል።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ጥፋት ኃይሎች ወጥመድ ላለመውደቅ በማስተዋል እየተጓዘ፤ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ከመንግሥት ጋር ተባበሮ ጥፋተኞችን ወደ ሕግ ለማቅረብ እና እንደዚህ ዓይነት ግድያዎች ፈጽመው እንዲቆሙ በትብብር ልንሠራ ይገባል። ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ኢትዮጵያ በመሥዋዕትነት የቆመች፤ በመሥዋዕትነት የምትቀጥል ሀገር ናት። በትብብርና በአንድነት መንፈስ የኢትዮጵያን ጠላቶች ደግመው እንዳይነሡ አድርገን ማጥፋት አለብን” ብለዋል።