ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያንና ጃፓን የታቀፉበት፣ “G7 ወይም የቡድን 7 ሀገራት” ተብሎ የሚታወቀው የሀገራት ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ በጋራ መግለጫ አውጥተዋል።
ባወጡት መግለጫ፣ “በኢትዮፅያ ሁሉም አካባቢ አመጽ እንዲቆም፣ ትግራይን ጨምሮ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተቀባይነት ያለው ተአማኒ ምርጫ እንዲካሄድ፣ ወደ ሰፊ ብሔራዊ እርቅ የሚወስድ ግልፅና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደት እንዲፈጠር” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የትግራይን ወቅታዊ ጉዳይ በተመለከተ “በቅርቡ ሪፖርት የተደረጉ በትግራይ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች እንዲሁም የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ ጥሰት በጣም አሳስቦናል” ያለው የቡድን 7 ሀገራቱ መግለጫ፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርስ ግድያን፣ ጾታዊ ጥቃቶችን እንዲሁም በትግራይ ነዋሪዎች እና የኤርትራ ስደተኞች ላይ የሚፈጸመውን አስገዳጅ መፈናቀል እንደሚያወግዝም አስታውቋል።
“ሁሉም ወገኖች የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ እና የሰብዓዊ መብቶችን እና ዓለም አቀፍ ህጎችን ማክበር አለባቸው” ሲልም አሳስቧል።
በቅርቡ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ “የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ይወጣሉ” በሚል የሰጡትንን መግለጫ በአዎንታዊ ጎኑ እንደሚቀበሉት በመግለጫው የጠቀሱት ሀገራቱ፣ ይህ ሂደት በፍጥነትና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈጸም እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡