ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ብሔርን መሠረት ያደረጉ ማንነት ተኮር የዘር ጭፍጨፋዎች እንዲቆሙ፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ እናት ፓርቲና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ዛሬ በራስ አምባ ሆቴል በሰጡት የጋራ መግለጫ ጠየቁ።
ፓርቲዎቹ በዜጎች ላይ ማንነታቸውን መሰረት አድርጎ የሚፈፀም ጥቃት እንዲቆም በጠየቁበት የጋራ መግለጫቸው፣ በሀገሪቱ ውስጥ በበርካታ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች እና በአጠቃላይ “መጤ” ተብለው በተፈረጁ ዜጎች ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተፈፀመ ያለውን ዘር ተኮር ጥቃት በጥብቅ እንደሚያወግዙ አስታውቀዋል፡፡
ፓርቲዎቹ “በሀገር አንድነት እና ደኅንነት ላይ የተጋረጠው አደጋ” አስቸኳይ መፍትሄ እንደሚያሻው በማመን የመፍትሄ አካል ለመሆን እና የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን፣ ለፌዴራል መንግሥትና የክልሎቹ አስተዳደሮች ባስተላለፉት መልዕክትም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገለፀዋል።
የችግሩን ግዝፈትና መደጋገም እንዲሁም በሀገሪቱ አንድነትና ደኅንነት ላይ የደቀነውን ከፍተኛ አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት ዘላቂ እልባት የመስጠቱ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለልተኛ ኮሚሽን በማቋቋም በጥልቀት መርምሮ ውጤቱንም ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡
“በተፈፀሙት ጥቃቶች ምክንያት ደጋፊ ወገኖቻቸውን ላጡና በጅምላ ተፈናቅለው ችግር ላይ ለወደቁት ወገኖች በአስቸኳይ የነፍስ አድንና የመልሶ ማቋቋም የተቀናጀ ርብርብ እንዲደረግ” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።