ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በፓርላማ የተናገሩት ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ ስራ፣ ዛሬ በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ ምርምር ማእከል ይፋ ተደርጓል።
ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂን በዓለም ከ56 አገራት በላይ ጥቅም ላይ እያዋሉት መሆናቸው በተገለፀበት የዛሬው መርሃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የዘርፉ ባለሙያዎችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ባስተላለፉት መልዕክት ” ደመና የማዝነብ ቴክኖሎጂ የሙከራ ትግበራ በስኬታማነት ተጠናቅቋል። ይህም ሀገራችን ከኃይል ማመንጫ እና መስኖ አንጻር የምትሠራቸውን ሥራዎች ተጨማሪ ዝናብ በማዝነብ መደገፍ እንደሚቻል ያመላክታል።
ከማለታቸውም በተጨማሪ ሀገርን ለማዘመን የሚደረጉ ይህን የመሳሰሉ ጥረቶች ላይ ማተኮር እንዲቻሎ አጥፊዎችን ለማጥፋትና ጥፋትን ለማስቆም መላው ሕዝባችን ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር መሥራት አለበት፤ የሀገራችን ዕድገት የአፍሪካም ዕድገት ነው። በሙከራ ሂደቱ የተሳተፋችሁ አካላት ምስጋናዬ ይድረሳችሁ” ብለዋል።
ደመናን የማዝነብ ቴክኖሎጂውን ለማሳካት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጓ ተነግሯል።