የኤርትራ ወታደሮች ትግራይን ለቀው እየወጡ ነው!

የኤርትራ ወታደሮች ትግራይን ለቀው እየወጡ ነው!

የG7 መግለጫ “እውነታውን ያላገናዘበ ነው” ተባለ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናመንግስት በትግራይ ከተጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ ጋር ተያይዞ በክልሉ የተከሰተውን ችግር ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
ሚኒስቴሩ ትናንት ባሰራጨው መግለጫ፣ “በሕወሓት ቀስቃሽነት ድንበር አቋርጠው የገቡት የኤርትራ ወታደሮች አሁን ለቀው መውጣት የጀመሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመከላከያ ኃይልም ድንበሩን በመቆጣጠር ላይ ይገኛል” ሲል ገልፆ፣ ከቀናት በፊት የቡድን 7 ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ “በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ያሳስበናል፤ የኤርትራ ወታደሮች በፍጥነት እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ” በሚል ያወጡት የጋራ መግለጫ፣ መንግስት በክልሉ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትንና መሬት ላይ ያለውን እውነታ በትክክል ያላገናዘበ መሆኑን አመልክቷል።

የቡድን 7 አባል ሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ የሰጡትን የጋራ መግለጫ ዝርዝር ነጥቦች በማስመልከት ከቀናት በፊት መዘገባችን ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት የፊንላንዱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሐቪስቶ “በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በተለይ የትግራይ ክልል ቀውስ እና በቀጠናው ባለው አንድምታ ላይ ለመወያየት” በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያቀኑ የአውሮፓ ህብረት አስታውቋል።

ሚኒስትሩ ከሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በኋላ፤ የተመለከቷቸውን ጉዳዮች የያዘ ሪፖርት በሚቀጥለው ወር ለሚካሔደው የአውሮፓ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ያቀርባሉ ተብሏል።
በዚሁ ጉዟቸው “ሁሉም ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡ፣ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ እና የስደተኞች መብቶች ጥበቃ ህግጋት እንዲያከብሩ እንዲሁም ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ገለልተኛ ምርመራ እንዲከናወን እንዲፈቅዱ” ጥሪ እንደሚያቀርቡ በመግለጫው ተመልክቷል።

LEAVE A REPLY