ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ ለሶስት የስራ ኃላፊዎች ሹመት መስጠታቸውን የጠቅላይ ሚ/ር ቢሮ ዛሬ አስታውቋል፡፡
ቢሮው በድረ ገፁ እንዳስታወቀው፣ አቶ መሐመድ ኢድሪስ መሐመድ – የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ረጋሳ – የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና አቶ ግዛው ተስፋዬ – የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከመጋቢት 27/2013 ዓ.ም ጀምሮ መሾማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተያያዘ፣ የብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ዛሬ የተሾሙት አቶ ዮናታን ተስፋዬ
ሹመታቸውን በሚመለከት ከሰዓታት በፊት በሰጡት መግለጫ፣ “ሀገራችን ለወጣቶች ምቹ ጥለናት የማንሰደድባት ሀገር አንድትሆን በተለያየ መንገድ ስታገል ነበር… ከአንድ ፓርቲ ውጭ ያለ አመለካከት ያለውን ሰው መግፋት እስከዛሬ ድረስ ያልጠቀመ አካሄድ በመሆኑ አሁን የተጀመረው አካሄድ የሚያስመሰግንና መንግስትና ፓርቲም የተለያዩ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው” ያሉ ሲሆን፣ አያይዘውም “አሁን በመንግስት አስተዳደር ላይ የተመደብኩበት ቦታ ላይ ሆኜ የተጀመረው የሪፎርም ስራ ግቡን እንዲመታ እንደ አንድ አጋዥ ሀይል ራሴን በመቁጠር ሀላፊነቴን በአግባቡ ለመወጣት ተነሰቻለሁ” በማለት ተናግረዋል።
አቶ ዮናታን ተስፋዬ በአንድነትና ሰማያዊ ፓርቲዎች ውስጥ በአመራር ደረጃ ተሳታፊ የነበሩና በፖለቲካ አቋማቸው ሳቢያ ለተደጋጋሚ እስር ሲዳረጉ የነበሩ መሆናቸው ይታወቃል።