በቱርክ የታሰረችው የበረራ አስተናጋጇ ሰላም እጅጉ ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል!

በቱርክ የታሰረችው የበረራ አስተናጋጇ ሰላም እጅጉ ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጇ ሰላም እጅጉ “ምንም በማታውቀው ጉዳይ በቱርክ ለእስር መዳረጓንና እድሜ ልክ እስራት ሊፈረድባት እንደሚችል” ታናሽ እህቷ ቤቴልም እጅጉ ከተናገረች በኋላ ጉዳዩ የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ትኩረት ስቦ በሰፊው ማነጋገሩን ቀጥሏል።

ነገሩ እንዲህ ነው፤ አንድ ቀን ጠዋት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ ወደ ሆነችው ሰላም እጅጉ ስልክ ይደወላል። በነጋታው ወደ ቱርክ ልትበር መሆኑን መስማታቸውንና ወደ አንካራ የሚሄድ መልእክት (እቃ) እንዳለ ከወዲያኛው ስልክ ያለች ትውልደ ኢትዮጵያዊት ታሳስባታለች ።

በበረራ አስተናጋጅነት በሚሰሩ ባለሞያዎች ዘንድ የማያውቋቸው ሰዎች ደውለው ይሄንን አድርሱልኝ መባባሉ የተለመደ ቢሆንም፣ ሰላም ነገር ግን ስለምትወስደው መልዕክት (ዕቃ) ማወቁ ተገቢ በመሆኑ መልሳ መላልሳ ጠየቀቻት “ምን አይነት እቃ ነው የማደርስልሽ? ኪሎውስ ስንት ነው?…”

ሁለት ትልልቅ ባህላዊ ስዕሎች መሆናቸውን ስትገልጽላት “ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ዕቃዎችን አድርሼ ስለማላውቅ ይቅርብኝ” ብትላትም ምንም ችግር እንደሌለውና ስዕሎቹን በተደጋጋሚ ጊዜያት በሌሎች ሰዎች እንደላከች እና አሁንም ከዚህ ቀደም ያደርሱላት የነበሩ ሰዎች (የበረራ አስተናጋጆች) ወደ ቱርክ በረራ ስለሌላቸው እና በዚህም የተነሳ ስዕሎቹን የሚገዟት የኢስታንቡል ደንበኞቿ በአስቸኳይ እንዳዘዟት ደጋግማ ትወተውታታለች።

በስተመጨረሻ እቃዎቹን እና የተቀባዮቹን አድራሻ በኮንትራት ታክሲ ትልክላታለች…እጅግ ትልልቅ የሆኑ በቆዳ ላይ የተሳሉ ባህላዊ ስዕሎች ናቸው። በማግስቱም ሰላም ከራሷ በላይ አስበልጣ የምትወደውንና የምትሳሳለትን የአንድ አመት ከሰባት ወር ትንሹን የበኩር ልጇን እና የትዳር አጋሯን ተሰናብታ ወደ ቱርክ ታቀናለች።

ሰላም ለወትሮው ወደ የትኛውም የዓለም ክፍል ስትሄድ ቀደማ የምታደርገው አውሮፕላኑ ልክ እንዳረፈ በሰላም መግባቷን ለቤተሰቦቿ ፈጥና ማሳወቅ ነበር።


የቱርኩ ጉዞ ግን ከዚህ የተለየ ሆነ። ይሄም የትዳር አጋሯን እና ቤተሰቦቿን እጅጉን ያስጨንቃቸዋል…ታዲያ በዚህ ጭንቅ ውስጥ ሆነው ነበር ሰላም ለባለቤቷ ደውላ እያለቀሰች የሆነውን ሁሉ የነገረችው። ከአዲስ አበባ ስትነሳ በማታውቃት ሴት የተሰጣት በቆዳ ላይ የተሳሉት ስዕሎች ህይወቷን በአንድ ጊዜ ወደ ገሃነብ ያወረዱት ስዕሎቹ የተቀቡት እጅግ አደገኛ የሆነውን አደንዛዥ ዕፅ (ኮኬይን) በመሆኑ በዚህም የተነሳ እስር ቤት ውስጥ እንዳለች እና እየደወለች ያለውም በፖሊሶች ስልክ መሆኑን ትገልፃለች።

በቱርክ ህግ መሰረት ደግሞ እንዲህ አይነት ወንጀል ሲፈፅም የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ ከ25 ዓመት እስከ 30 ዓመት እስራት የሚፈረድበት ሲሆን፣ የሰላምን ጉዳይ የሚከታተለውን ጠበቃም ቤተሰቦቿ ደውለው አነጋግረውት ነበር። ጠበቃዋም በድጋሚ ፍርድ ቤት ከመቅረቧ በፊት የመጀመሪያ ክፍያ 7000 (ሰባት ሺ) ዶላር ካልተከፈለው ጥብቅና ሊቆምላት እንደማይችል ነግሯቸዋል። ላለፉት አስራ አምስት ቀናት እስር ቤት ውስጥ የምትገኘዋ የሰላም ጠበቃ በቀጣይ የክፍያውም ሁኔታ እንደምትከሰስበት ክስ ክብደት ይወሰናል ብሎአቸዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላለፉት 7 አመታት በበረራ አስተናጋጅነት ትሰራ የነበረችው እህታችን ሰላማዊት እጅጉ በስራዋ ታታሪና በኢትዮጵያ ጨዋነት ያደገች ባለ ትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ እናት ስትሆን ባላሰበችውና ባልገመተችው መልኩ በክፉዎች ወጥመድ ውስጥ ወድቃ በአሁኑ ሰዓት የማትወጣው ማጥ ውስጥ ገብታለች። በቀጣይም የሞት ፍርድ ወይም የእድሜ ልክ እስራት ይጠብቃታል።

ይህ በመሆኑም መላው ቤተሰቧ “በቱርክ ሃገር (ኢስታንቡል )እምትገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በምትችሉት ሁሉ ከእህታችን ጎን እንድትቆሙና ህይወቷን እንድትታደጉ በፈጣሪ ስም እለምናችኋለሁ። በቱርክ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንስላ ሰራተኞች እህታችን ሰላም እጅጉ የምትገኝበትን ሁኔታ ሄዳችሁ እንድትከታተሉ እና ኢትዮጵያዊነታችሁን በተግባር እንድታስመሰክሩ በትህትና እጠይቃችኋለሁ። ለእህታችን ጥብቅና ለሚቆምላት ባለሞያ ክፍያ ይሆን ዘንድ በአሜሪካን ሃገር ጎ ፈንድ ሚ የተከፈተ ሲሆን፣ በዚያ ያላችሁ የአቅማችሁን እንድትረዱና ሰላምን ከሞት እንድትታደጓትና ከቤተሰቧ ጋር እንድትቀላቀል በማድረግ የራሳችሁን አስተዋፅኦ እንድታበረክቱ እያልኩ በሃገር ውስጥ ያላችሁ ደግሞ እህታችንን ለመደገፍ በማቲያስ ጌታቸው፣ ቤተልሔም እጅጉ እና አበባ ገ/ጊዮርጊስ ስም በተከፈተው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባልዳራስ ቅርንጫፍ ሒሳብ ቁጥር 1000393194948 ድጋፋችሁን እንድታደርጉ በፈጣሪ ስም እንለምናችኋለን” የሚል ልመናና ተማፅኖ እያቀረቡ ይገኛሉ።

LEAVE A REPLY