የሱማሌ ክልል መንግስት ዛሬ በንፁሃን ላይ ጥቃት መድረሱን መረር ባለ መግለጫ አወገዘ!

የሱማሌ ክልል መንግስት ዛሬ በንፁሃን ላይ ጥቃት መድረሱን መረር ባለ መግለጫ አወገዘ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት “ዛሬ መጋቢት 28-2013 ዓ.ም ጠዋት የአፋር ክልል ልዩ ፖሊስ ኡጉጉማ ከሚባለው የሽብር ክንፉ ጋር በመቀናጀት በአራት የክልላችን ቀበሌዎች ግድያዎችና እንግልት መፈፀሙን ተከትሎ ነው ክልሉ ጠንከር ያለ መግለጫ የወጣው።

በደዋዲድ፣ በገውረአን፣ በቀላሌና በደንለሄ ላይ መጠን ስፊ ጥቃት በመፈፀም ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ንፁሀንን ገድለዋል” በማለት ባወጣው መግለጫ፣ “በክልላችን ነዋሪዎች ላይ የሚደርሰውን ሞት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ለመከላከል ማንኛውንም አስፈላጊ እርምጃ ለመውሰድ የምንገደድ መሆኑን እያሳወቅን ጉዳዩ ወደለየለት ግጭት ከማምራቱ በፊት የአፋር ክልል መንግስት ቆም ብሎ ማሰብ እንዲጀምርና የፌደራል መንግስትም የመፍትሔው አካል ለመሆን እንዲሰራ በጥብቅ ለማሳሰብ እንወዳለን” ብሏል።

የክልሉ መንግስት ከሰአታት በፊት ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በክልላችን ነዋሪዎች ላይ እያደረሰ ያለውን ግድያና ማፈናቀል አስመልክቶ ከሱማሊ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ!

በቅድሚያ ባለፈዉ አርብ መጋቢት 24 – 2013 ዓ.ም ደአዋዲ እና ቀረፋ በተባሉ ቀበሌዎች ላይ እንዲሁም ዛሬ መጋቢት 28 ጠዋት በደዋዲድ ፣ በገውረአን ፣ በቀላሌና በደንለሄላይ በሚባሉ አራት የክልላችን ቀበሌዎች በሚኖሩ ንፁሃን ነዋሪዎች ላይ በአፋር ክልል ልዩ ሀይል በተፈፀመው ግድያ፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልፃለን።
በአንድ በኩል የውስጥና የውጪ ፀረ ኢትዮጵያ ሀይሎች ተቀናጅተው የአገራችንን ህልውና እየፈተኑ ባሉበት ፤ በሌላ በኩል አገር ወዳድ ሀይሎች ሰላማዊና ፍትሀዊ ምርጫ በማድረግ አገር ለማሻገር ጥረት እያደረጉ ባለበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የአፋር ክልል መንግስት በየእለቱ እያደረገ ያለው የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ የክልሉ መንግስት አሰላለፍ ከየትኛው ወገን እንደሆነ እንድንጠራጠርና እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ሆኖ አግኝተነዋል።
የአፋር ክልል መንግስት በሰመራ እና በአዋሽ መካከል ሱማሌ መኖር የለበትም በሚል ከንቱ ፍላጎት እየተመራ ነዋሪዎችን በመግደል፣ ንብረታቸውን በማውደምና በማፈናቀል ለአመታት አካባቢው ሀዘን የማይለየው የሰቆቃ ምድር እንዲሆን ሲያደርግ ቆይቷል።
ባለፈው አርብ መጋቢት 24-2013 ዓ.ም በአፋር ክልል ልዩ ፖሊስ እና በክልሉ መንግስት በሚደገፈው ኡጉጉማ በሚባለው አሸባሪ ቡድን የተቀናጀ ጥምረት በንፁሃን የአካባቢው ነዋሪ ዜጎች ላይ ጉዳት ቢደርስም የሱማሊ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለሰላምና ለአገር አንድነት ሲባል ጉዳዩ በትእግስትና በሰከነ መንገድ መያዝ እንዳለበት በማመን ስለተፈጠረው ሁኔታ መግለጫ ከማውጣትና ወደሚዲያ ከመውሰድ ተቆጥቦ ቆይቷል።
በኛ በኩል በአስተዋይነትና በአርቆ አሳቢነት ያለንበትን አገራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት የተወሰደውን የዝምታ አማራጭ የአፋር ክልል መንግሥት እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ መግደልና ማፈናቀሉ ሳያንስ ስግብግብ ፍላጎቱን ለማሳካት የፈፀመውን አስነዋሪ ተግባር እኛ እንደፈፀምነው አድርጎ በሚዲያ በማቅረብና ቀድሞ በማልቀስ የማሳሳት ሙከራ አድርጓል።
ይሁን እንጂ የአፋር ክልል መንግስት ለአመታት ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉ በተለይም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጣቢያዎችን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ
በእቅድ የተመራ አካባቢውን የማተራመስ የጥፋት ተግባሩን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በዚህም
ባለፋው አርብ መጋቢት 24-2013 ዓም ደአዋዲ እና ቀረፋ በተባሉ ቀበሌዎች በኑፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት በመፍፀም ከ 25 በላይ አርብቶ አደሮች ሲገደሉ ከ 30 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ንብረትም ወድሟል ።
በተመሳሳይ ዛሬ መጋቢት 28-2013 ዓ.ም ጠዋት የአፋር ክልል ልዩ ፖሊስ ኡጉጉማ ከሚባለው የሽብር ክንፉ ጋር በመቀናጀት በአራት የክልላችን ቀበሌዎች ማለትም በደዋዲድ፣ በገውረአን ፣ በቀላሌና በደንለሄ ላይ መጠን ስፊ ጥቃት በመፈፀም ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ንፁሀንን ገድለዋል።
የአፋር ክልላዊ መንግስት ከውስጥና ከውጪ ሆነው
የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማወክ እንደሚሰሩ ሀይሎች ሁሉ የአካባቢው ነዋሪዎች አንድነትና ትብብር እንዳይጠናከር በየጊዜው ጥቃት በመፈጸም አካባቢው የሁከት ቀጠና እንዲሆን የማድረጉን ተግባር አጠናክሮ ቀጥሎበታል።
በመሆኑም የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ለአገር ሰላም ዋጋ በመስጠትና ለህዝቦች አንድነት በማሰብ እስካሁን ህዝባችን እየሞተና እየተሰቃየም ቢሆን ጉዳዩን በትእግስትና በማስተዋል ሲከታተለው ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ያንድ ወገን ጥረት ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ ስለማይችል በቀጣይ በክልላችን ነዋሪዎች ላይ የሚደርሰውን ሞት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ለመከላከል ማንኛውንም አስፈላጊ እርምጃ ለመውሰድ የምንገደድ መሆኑን እያሳወቅን ጉዳዩ ወደለየለት ግጭት ከማምራቱ በፊት የአፋር ክልል መንግስት ቆም ብሎ ማሰብ እንዲጀምርና የፌደራል መንግስትም የመፍትሔው አካል ለመሆን እንዲሰራ በጥብቅ ለማሳሰብ እንወዳለን።
መጋቢት 28-2013 ዓ.ም
የሶማሊ ክልላዊ መንግስት -ጅግጅጋ

 

LEAVE A REPLY