ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– “የማንዶሊኑ ንጉስ” እና “አየለ ማንዶሊን” በሚሉ ቅጥያ የክብር ስሞች የሚጠራው አንጋፋው ድምፃዊ፣ የዜማ እና የግጥም ደራሲ፣ ሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች አየለ ማሞ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ዛሬ መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ/ም ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።
በሃገራችን ኢትዮጵያ በሙዚቃው ዘርፍ ታላቅ አስተዋፅኦ እያደረጉ ካሉት የሙዚቃ ስዎች አንዱ የነበረውና ብቸኛው የማንዶሊን ተጫዋቹ ሙዚቀኛ አየለ ማንዶሊን፣ ክብር ዘበኛ የሙዚቃ ክፍልን ለ34 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ የግጥምና ዜማ ፈጠራዎቹን ከሰጣቸው አንጋፋና ወጣት ድምፃውያን መካከልም፤ ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ፣ መሐሙድ አህመድ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ኩኩ ሰብስቤ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ሀመልማል አባተ፣ ብፅአት ስዩም፣ ወረታው ውበት፣ አስቴር ከበደ፣ እያዩ ማንያዘዋል፣ ሻምበል በላይነህ፣ ደረጀ ደገፋው፣ ጌታቸው ጋዲሳ፣ ህብስት ጥሩነህ፣ ምንያህል ጥላሁን ገሠሠ፣ ውብሻው ስለሺ፣ መንበረ በየነ፣ ትዕግስት ይልማ፣ ከበቡሽ ነጋሽ (ሚሚ)፣ ገነነ ኃይሌ፣ ጌታቸው ተካ፣ ዓለማየሁ ግዛው… ይገኙበታል።
ሙዚቀኛ አየለ ማሞ ከዚህም በተጨማሪ፣ ራሱ ማንዶሊን የሙዚቃ መሳርያ እየተጫወተ “ወይ ካሊብሶ፣ የኔውብ አይናማ፣ “ያለሰለሴ ባዬቲ (ኦሮምኛ) እና “እማማ ድንብሎ” የተሰኘ የጉራጊኛ ዘፈኖቹን ለአድማጭ አቅርቧል።
ጥር 12 ቀን 1934 ዓ.ም የተወለደው ሙዚቀኛ አየለ ማንዶሊን በተወለደ በ79 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶናል። ሥርዓተ ቀብሩም ነገ መጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ይፈፀማል።
ዝግጅት ክፍላችን በጋሽ አየለ ዜና እረፍት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና ለመላ የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናቱን ይመኛል።