ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሶማሌ ክልል ስር በሚገኙ አራት ቀበሌዎች ላይ ማክሰኞ በተሰነዘረ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መገደላቸውንና ጥቃቱን የሰነዘሩት “የአፋር ክልል ልዩ ኃይል እና አጉጉማ የሚባል ታጣቂ ቡድን ነው” ሲል
የሶማሌ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የወነጀለ ሲሆን፣ የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ “ደረሰ የተባለው ጥቃት ከእውነት የራቀ ነው” በማለት ክልሎቹ እርስ በርስ መወነጃጀላቸውን ቀጥለዋል። ይሁንና፣ በአፋር እና ሶማሌ ክልል መካከል የተፈጠረው ግጭት ተባብሶ የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ መሆኑንና ቁስለኞችም ከቀን ወደቀን እየጨመሩ ከህክምና አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ያመለከቱት የሃይማኖት መምህሩ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ “የሁለቱ ክልል መሪዎች በአፋጣኝ ወደንግግር መጥተው ግጭቱን ሊያስቆሙ ይገባል፤ ሁለቱንም ክልሎች የሚያስተዳድሩት ኃላፊዎች ያላቸው ስብእና እና የፖለቲካ ተቀባይነት መሰል ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ከምንግዜውም በላይ የሚያስችላቸው በመሆኑ በፍጥነት ወደጠረጴዛ ሊመጡ ይገባል” ሲሉ ጠይቀዋል።
“ባህላዊ እና ኃይማኖታዊ የግጭት መፍቻ መንገዶችም እድል ሊሰጣቸው ይገባል” ያሉት ኡስታዝ አቡበክር፣ “የፌዴራል መንግስት ቸልተኝነት ለግጭቱ መባባስና ለንፁሃን ሞት የራሱን ሚና እየተወጣ ይገኛል” ሲሉ ወቅሰዋል።
የክልሎቹ መሪዎች ፈቃደኝነት ካለ በግል ሆነ በቡድን ለሚደረጉ የግጭት መፍቻ ጥረቶች የድርሻቸው ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸው በመግለፅም “ለአስርት አመታት በሄድንበት መንገድ እየሄድን ሰላም እንደማይመጣ በመረዳት የክልሎቹን ህዝቦችና መሪዎች ወደ መፍትሄ እንዲመጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።